ቀጥታ፡

ከኢትዮጵያ ተሰርቆ ወደ ውጭ አገር ተወስዶ የነበረ ዘውድ ተመለሰ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2012(ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኢትዮጵያ ተሰርቆ ወደ ውጭ አገር ተወስዶ የነበረውን ዘውድ  ለመመለስ ከመጡ የኔዘርላንድስ የውጪ ንግድና የልማት ትብብር ሚኒስትር ሲግሪድ ካግ ጋር  ተወያይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዘውዱ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ላመቻቹት ለአቶ ሲራክ አስፋውና ለኔዘርላንድስ መንግስት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የ18ኛ ክፍለ ዘመን ዘውድ እንደነበር የተነገረለት የኢትዮጵያ ቅርስ ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ ተሰውሮ ቆይቷል። ሆኖም በጥቅምት 2011 ዓ.ም. በኔዘርላንድስ ሮተርዳም ከተማ ሊገኝ ችሏል። የኔዘርላንድ መንግሥት ይህንን ቅርስ ለኢትዮጵያ መመለስ ጠቃሚ እንደሆነ በማመን ዘውዱ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። በዛሬው እለትም የተሰረቀው ዘውድ ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት አስታውቋል። ዘውዱ ለኢትዮጵያ እንዲመለስ ያደረጉት ለ41 ዓመታት በኔዘርላንድስ የኖሩት አቶ ሲራክ አስፋው ለአገራቸው ያላቸው ፍቅርና ታማኝነት ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም