83ኛዉ የየካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
83ኛዉ የየካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን ተከበረ
አዲስ አበባ የካቲት 12/2012 ( ኢዜአ) በአዲስ አበባ 83ኛዉ የየካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከበረ። በበዓሉ ዝግጅት ላይ የጥንታዊ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር እንዳወቅ አብቴና በኢትዮጵያ የሰርቢያ አምባሳደር አሌክሳንደር ሪስቲች ተገኝተዋል። ከአዲስ አበባ ቀይ መስቀል ማኅበርና ከአዲስ አበባ አረጋዉያን ማኅበር እና ሌሎች የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሃላፊዎች በበዓሉ ተገኝተዋል። የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት ማርሽ ባንድ ልዩ ልዩ ኅብረ ዝማሬ ያሰሙ ሲሆን ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተገኙ ተማሪዎችም በበዓሉ ላይ ተካፋይ ነበሩ። የዛሬ 83 ዓመት በ1929 ዓ.ም በጣሊያን ጦር ዳግም ወረራ በአዲስ አበባና በደብረ ሊባኖስ ገዳም በኢትዮጵያ ሰማይ ስር አሳዛኝ ታሪክ ተፈጽሞ ማለፉ ይታወሳል። በወቅቱ የጦሩ መሪ ግራዚያኒ በቀድሞው ገነተ ልዑል ቤተ-መንግሥት በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለኢትዮጵያ ህዝብ ስጦታ እሰጣለሁ በሚል በተሰበሰበበት ወቅት በሞገስ አስገዶምና አብርሃ ደቦጭ የእጅ ቦንቦች ተወረወሩ። በጥቃቱ ግራዚያኒን ጨምሮ የጣልያን ጦር አመራሮች ጉዳት ደረሰባቸው ይህን ተከትሎም በግራዚያኒ የሚመራው የጣሊያን ጦር በወሰደው የአጸፋ ርምጃ ጾታና ዕድሜ ሳይለይ ኢትዮጵያዊያንን ገደለ አቆሰለ። የታሪክ ድርሳናት እንደሚያሳዩትም በዕለቱና በነበሩት ተከታታይ ሁለት ቀናት ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን መስዋዕት ሆነዋል። የጣሊያን ጦር በአዲስ አበባ ሳያበቃ ቦንብ በመወርወር ጥቃት ያደረሱበት ወጣቶች ተሸሽገውበታል ብሎ በጠረጠራቸው ቦታዎች በተለይም በደብረሊባኖስ ገዳም አሰቃቂ ጥቃት ፈጽሟል። ይህንን ቀን ለመዘከር ስድስት ኪሎ ሰማዕታት አደባባይ አባት አርበኞች በተገኙበት ዛሬ ስነ-ስርዓት ተካሂዷል።