ቤተ-ክርስቲያን ህገ-ወጥ የአምልኮ ቦታ ነው በሚል በተወሰደ እርምጃ ህይወታቸውን ላጡ ምዕመናን ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠየቀች - ኢዜአ አማርኛ
ቤተ-ክርስቲያን ህገ-ወጥ የአምልኮ ቦታ ነው በሚል በተወሰደ እርምጃ ህይወታቸውን ላጡ ምዕመናን ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠየቀች
አዲስ አበባ የካቲት 11/2012 (ኢዜአ) በቅርቡ በአዲስ አበባ ህገ-ወጥ ነው በሚል ቤተ-ክርስቲያን ለማፍረስ በተወሰደው እርምጃ ህይወታቸው ላለፉ ምዕመናን ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ጠየቀች። ቤተ-ክርስቲያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሰሞኑ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለሚኖሩ ምዕመናን የቤተ-ክርስቲያን መስሪያ ቦታ በማስፈቀዳቸው አመስግናለች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሲያካሄድ የነበረውን አስቸኳይ ጉባኤ ዛሬ አጠናቅቆ የአቋም መግለጫ አውጥቷል። በመግለጫው ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም ሌሊት በቦሌ ቅዱስ ገብርኤልና ቅድስት አርሴማ ቤተ-ክርስቲያን ህገ ወጥ ይዞታ ነው በሚል የጸጥታ አካላት በወሰዱት እርምጃ የዜጎች ህይወት ማለፉን አስታውሶ ድርጊቱን የፈፀሙት ለህግ እንዲቀርቡና የምርምራ ውጤቱም ለምዕመኑ ይፋ እንዲደረግ ሲኖዶሱ ጠይቋል። ከዚህ በተጨማሪ ቤተ-ክርስቲያኗ ቦታ ተሰጥቷት ቤተ-ክርስቲያን መገንባት እንድትችልም ሲኖዶሱ ጠይቋል። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ካህናትና ምዕመናን ከእስር እንዲፈቱም ነው ቅዱስ ሲኖዶሱ የጠየቀው። በተጨማሪ በአንዳንድ የቤተ-ክርስቲያኗ ገዳማት ላይ ችግር የሚፈጥሩ ግለሰቦች በመንግስት እርምጃ እንዲወሰድባቸው ሲኖዶሱ መጠየቁን ቅዱስ ፓትሪያርኩ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በመግለጫው ገልጸዋል። አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያደርሱ ዘገባዎችን እያቀረቡ መሆኑንና ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስበዋል። መንግስትም በጉዳዩ ዙሪያ አስፈላጊውን ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ቅዱስ ሲኖዶስ መጠየቁን አመልክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሰሞኑ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ባደረጉት ጉብኝት በአገሪቱ የሚኖሩ ምዕመናን የቤተ ክርስቲያን መስሪያ ቦታ በማስፈቀዳቸው ቅዱስ ሲኖዶሱ ምስጋና አቅርቧል። የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን ጠብቆ በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍንና ወደምንመኘው የእድገት ደረጃ እንድንደርስ ህዝቡ በጋራ ጸንቶ መቆም ይገባዋል ሲልም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤው ጥሪ አቅርቧል።