የብልጽግና እሳቤ ልማትን የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን ልማትን የሚፈጥር ዜጋ ማፍራትን የሰነቀ ነው-- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ - ኢዜአ አማርኛ
የብልጽግና እሳቤ ልማትን የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን ልማትን የሚፈጥር ዜጋ ማፍራትን የሰነቀ ነው-- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ
አዲስ አበባ የካቲት 11/2012 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የብልጽግና እሳቤ ልማትን የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን ልማትን የሚፈጥር ዜጋ ማፍራትን የሰነቀ መሆኑን ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተወጣጡ የስልጤ ዞን ነዋሪዎች ጋር በወራቤ ከተማ ውይይት አድርገዋል። ነዋሪዎቹ በመሰረተ ልማት ሰላምና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል። በተለይ የውሃ፣ መንገድና መብራት መሰረተ ልማት ጥያቄዎች ሰፊውን ድርሻ ወስደው በነዋሪዎቹ ተነስተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው በብልጽግና እሳቤ ልማትን የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን ልማትን የሚፈጥር ዜጋ እንዲኖር በትኩረት እንደሚሰራ ነው የተናገሩት። ቁሳዊ እድገት በአእምሮ ልማት ካልተመራ ብልጽግናን እውን ማድረግ ፈታኝ መሆኑንም አስረድተዋል። ከቆሸ ቢላሎ ድረስ ደረጃውን በጠበቀ አስፓልት ለመገንባት በነገው እለት የኮንትራት ስምምነት እንደሚፈረምም አረጋግጠዋል። መብራት በተለያያ የኢትዮጵያ ከተሞች የሚስተዋል ችግር መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከዋና መስመር ውጭ የሆኑ የሃይል አማራጮችን (በኦፍ ግሪድ) ለማልማት እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል። የስልጤ ተወላጅ ባለሃብቶች ከመንግስት ጋር በሽርክና በመስራት አጋርነታቸውን ማሳየት እንደሚችሉም አብራርተዋል። መንግስት ከዓለም ባንክ ጋር በመሆን ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ የ100 ከተሞችን የውሃ ችግር ለመፍታት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ነው የጠቀሱት። በደቡብ ከልል እየተነሳ ያለውን የአስተዳደራዊ ወሰን ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታት የአካባቢውን ተወላጆች ያካተተ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በመሆኑም መንግስት የያዘው የብልጽግና ሃሳብ እውን እንዲሆን ዜጎች እልቂትን ከሚጭሩ የጥቅመኛ ፖለቲከኞችና ግለሰቦች ቅስቀሳ ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።