ወጣቱ ትውልድ ለሀገር ሰላምና ዕድገት ተግቶ እንዲሰራ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ ትውልድ ለሀገር ሰላምና ዕድገት ተግቶ እንዲሰራ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሰበ
ድሬዳዋ (ኢዜአ) የካቲት 11 /2012 ዓም ወጣቱ ትውልድ የሀገሪቱን ህብረትና አንድነት ለማናጋትና ሰላምን ለማደፍረስ ድብቅ አጀንዳ አንግበው የሚንቀሳቀሱ አካላትን በተቀናጀ መንገድ መከላከል እንዳለበት የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሰበ። የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በድሬዳዋ አስተዳደርና ሐረሪ ክልል ከሚገኙ የኃይማኖት ተቋማት ለተውጣጡ ወጣቶች በክርስቲያንና ሙስሊም ህብረተሰብ ግንኙነትና ህብረት ላይ ያተኮረ የሁለት ቀናት የውይይት መድረክ ዛሬ በድሬዳዋ ተጀምሯል ፡፡ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀኃፊ ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ በመክፈቻው ስነ ስርዓት ላይ እንደተናገሩት ኃይማኖትንና ብሔርን ተገን አድርገው የሀገር ሰላምና ልማትን በማደፍረስ ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት የሚሯሯጡ አካላት በተቀናጀ መንገድ መመከትና መከላከል ይገባል ፡፡ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ህብረቱንና አንድነቱን ጠብቆ የሀገሪቱን ሰላም በአስተማማኝ መንገድ የመጠበቅ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ህዝቦች ለዓመታት ተከባብረው፣ ተዋደውና ተጋምደው የኖሩባትን ሀገር መጠበቅ የሁሉም ኃላፊነት ነው ያሉት ጠቅላይ ፀኃፊው ያለችን አንዲት ሀገር ወጣቱ በቁርጠኝነት ሊጠብቃት ይገባል ብለዋል፡፡ ወጣቱ ትውልድ የማንም የፖለቲካና የድብቅ ፍላጎት ማራመጃ እንዳይሆን በሰከነ አእምሮ ራሱንና መሰሎቹን በመጠበቅ ለሀገር የሚተርፍ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ እንዲረባረብ መልእክት አስተላልፈዋል ። የድሬዳዋ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪ መምህር ያሬድ ዘውዱ በበኩላቸው ለሁለት ቀናት የሚካሔደው የውይይት መድረክ ዓላማው በወጣቶች መካከል ያለውን የሰላም ተልዕኮ በማፅናት በየአድባራቱ፣ በየመስጅዱና በየአምልኮ አጥቢያው የተረጋጋ ሰላማዊና ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ነው ። በተለይም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በክርስትናና በእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል የሚታየውን የትብብርና የህብረት ተግባራት በማጽናት በሃይማኖት ሽፋን የሚካሔዱ አፍራሽ ተግባራትን በጋራ ለመመከት የውይይት መድረኩ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አስረድተዋል ። በውይይቱ ላይ ከ70 በላይ ከድሬዳዋና ከሐረር የተውጣጡ የኃይማኖት ተቋማት መሪዎችና ወጣቶች ጉባኤ ተሳታፊ ሆነዋል ።