የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ውጤታማ መሆን አለመቻሉ ተነገረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ውጤታማ መሆን አለመቻሉ ተነገረ
አዲስ አበባ ሰኔ 20/2010 ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች ለአፈፃፀሜ ዝቅተኛነት ምክንያት ሆነውብኛል ሲል የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ። ኮርፖሬሽኑ የ11 ወራት የስራ አፈፃፀሙን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገምግሟል። ኮርፖሬሽኑ እንደ አዲስ ከተቋቋመበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በመንግስት ከሚሰጡትና በግሉ ተጫርቶ ከሚያገኛቸው ፕሮጀክቶች የመንገድ ፣ የግድብ፣ የቦይ፣ የደረቅ ወደብ የህንፃና የመስኖ ልማት ግንባታዎችን ያከናውናል። በተመሳሳይ ተቋሙ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚሆኑ ግብዓቶችን በማምረትና ከውጪ በማስገባት በዘርፉ ለተሰማሩ ድርጅቶች በማቅረብ የገበያ ክፍተትን እንደሚሞላ ተጠቅሷል። ሆኖም በራሱ ተቀብሎ የሚሰራቸው ስራዎች አፈፃፀም ተቋሙ በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መድረስ ከሚገባው አንፃር ሲወዳደር ክፍተቶች እንዳሉበት ሪፖርቱ ያስረዳል። ለአብነትም ደብረ ብርሃን የታሸገ ውሃ ማምረቻ ፋብሪካና ቦሌ ቡልቡላ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ በአመቱ ከተያዘላቸው እቅድ አንፃር አፈጻጸማቸው ከሩብ በታች መሆኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል። በሌላ በኩል የኩራዝ ስኳር ፋብሪካና ዋና ቦይ ግንባታ ስራዎች፣ የወልቃይትና አርጆ ደዴሳ ስኳር ልማት የመስኖ ስራዎች፣ ማዞሪያ-ሃዴሮ (ዱራሜ ከተማን ጨምሮ)፣ አዳማ- አዋሽ የመንገድ ግንባታ ስራዎች አፈፃፀማቸው ከግማሽ በታች መሆኑም ተጠቅሷል። የኮርፖሬሽኑ የ11 ወራት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ህንፃ ግንባታ ስራዎች አፈፃፀምም ከሰላሳ ሰባት በመቶ እንዳልዘለለ በሪፖርቱ ተመልክቷል። የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ኃይለመስቀል ተፈራ እንደሚሉት ለፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም ክፍተት ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል። ከውጫዊ ምክንያቶቹ ደምበኞች ክፍያ በወቅቱ ስለማይከፍሉ በገንዘብ እጥረት ሳቢያ ሌሎች ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ዕቅድ መሰረት ማከናወን አለመቻሉን ገልፀዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች የነበረው የፀጥታ መታወክም ስራዎችን በወቅቱ ለማከናወን አላስቻለም ብለዋል። በአሰሪዎች በኩል የተሟላ ዲዛይን ያለመስጠት፣ በየጊዜው ዲዛይን መለዋወጥና መሻሻል ሌላኛው የውጪ ችግር እንደነበርም ጠቅሰዋል። ከውጪ የሚገቡ ግብዓቶችን ለማስገባት በዚህ አመት የነበረው የውጭ ምንዛሪ እጥረትም በምክንያትነት ተቀምጧል። በመንገድ፣ በግድብና በመስኖ ልማት አካባቢ የታዩ የወሰን ማስከበር ችግሮችና የክረምቱ ቀድሞ መግባትም ስራዎች በተያዘላቸው ጊዜ ላለመከናወናቸው ምክንያት ሁኗል ብለዋል። በውስጥ የባለሙያዎች የአቅም ውሱንነት መኖሩንም ገልጸዋል። ዋና አስፈፃሚው እንደሚሉት ችግሮቹን ለማስተካከል የሰው ኃይልን ከማብቃት ጀምሮ የተለያዩ ስልጠናዎችን መስጠት ጀምረዋል። በተጨማሪም ከውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ፣ ከብረታ ብረት ኮርፖሬሽን፣ ከስኳር ኮርፖሬሽንናከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ለማስከፈል በሂደት ላይ ነን ብለዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ ተቋሙ ላይ እየታዩ ያሉ የፕሮጀክቶች መጓተትና በተቋሙ የሚታዩ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶች መስተካከል እንዳለባቸው አሳስቧል። በ2011 ዓ.ም ያሉትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ያልተሰሩ ስራዎችን ማካካስና ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ አሰራሮች መዘርጋት እንዳለበትም አስገንዝቧል።