ቀጥታ፡

ጠል ሰም - ትኩረት ያልተሰጠው የስዕል ጥበብ

አዲስ አበባ የካቲት 11/2012 ( ኢዜአ) ጠል ሰም በኢትዮጵያ የስዕል ጥበብ ውስጥ ትኩረት ተሰጥቶት ጥናት እየተደረገበት እንዳልሆነ ተገለፀ። ሕብረተሰቡ ለዚህ የስዕል ጥበብ ያለው እውቀት ውስን ከመሆኑ ባሻገር በመጥፎ ጎኑ እየተረዳው እንደሆነም ነው የተገለጸው። የጠል ሰም የስዕል ጥበብ ጥንታዊያን አባቶች በሕክምናና ሥነ-ፈለግ ምርምር የደረሱበትን ውጤት ለመግለጽ የሚጠቀሙበት አገር በቀል የአሳሳል ዘይቤ እንደሆነ ይነገራል። በጥበቡ ላይ ላለፉት 10 ዓመታት ጥናትና ምርምር ያደረገው ሠዓሊ ሳምሶን ከበደ እንደገለፀው፣ ይህ ጥበብ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ቢኖርም ከአንዳንድ ትልልቅ ገዳማትና ከተወሰኑ ሰዎች በቀር ተገቢ ትኩረት ሲሰጠው አይታይም። ለዚህ አገር በቀል የስዕል ጥበብ ዘርፍ ትኩረት ካለመሰጠቱ ባሻገር የኅብረተሰቡ ግንዛቤ የተዛባ መሆኑን ያመለከተው ሰዓሊው ይህንን አመለካከት ለመቀየር መነሳቱን ገልጿል። ሰዓሊ ሳምሶን እንዳለው በህብረተሰቡ ዘንድ የጠል ሰምን የስዕል ጥበብ ከጥንቆላ ጋር የማያያዝ የተሳሳተ ግንዛቤ አለ። ነገር ግን ጥበቡ የጥንት አባቶች በሕክምናና ሥነ-ፈለግ ምርምር የደረሱበትን ውጤት የሚገልጹበት የአሳሳል ዘይቤ መሆኑን አስረድቷል። ይህ የስዕል ጥበብ ዘርፍ በክርስትና ብቻ ሳይሆን በሌሎች እምነቶችም የራሱን መልክ ይዞ እንደተቀመጠ የሚናገረው ሳምሶን ስዕሉን ለማስተዋወቅ የራሱን ስዕሎች በመሳል ለእይታ ማቅረቡን ገልጿል። የስዕል ጥበቡ በሌሎች ዓለማት ቢኖርም የኢትዮጵያ የጠል ሰም የስዕል ጥበብ መነሻው መጽሐፈ ሄኖክ መሆኑን ሰዓሊው አስረድቷል። የስዕል ጥበብ ዘርፉን ለመመርመር ጥረት ቢያደርግም ሀሳቡን ለሌሎች ለማስረዳት የአቅም ውስንነት እንቅፋት እንደሆነበትም ነው የገለጸው። እንደ ሰዓሊው ገለጻ በ"ሌላ አርት ጋለሪ" ለእይታ ባበቃቸው የጠል ሰም የሥዕል ሥራዎች ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ አገራት ከመጡ ጎብኚዎች በጎ ምላሽ አግኝቷል። በጋለሪው የጠል ሰም ስዕሎችን ለተወሰኑ ጊዜያት ያቀረበበት ዋነኛ ምክንያት ስለ ጥበቡ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር መሆኑንም አስረድቷል። በሰዓሊ ሳምሶን ከበደ በ"ሌላ አርት ጋለሪ" ከጥር 16 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለእይታ የቀረቡት የጠል ሰም ስዕሎች እስከ የካቲት 21 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ለህዝብ ክፍት ሆነው ይቆያሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም