ቀጥታ፡

በቃሎጂ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች የዕለት ደራሽ ምግብ በወቅቱ አይደርሳቸውም- የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም

አዲስ አበባ የካቲት 11/2012 ( ኢዜአ) በሶማሌ ክልል ቃሎጂ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች የዕለት ደራሽ ምግብ በወቅቱ እየደረሳቸው አይደለም ሲል የኢትዮጵያ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ። ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ የዕለት ደራሽ ምግቡ የዘገየው በጸጥታ ችግር ምክንያት ነው ብሏል። የተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ባለፉት ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በነበሩ የጸጥታ ችግሮች ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ያወሳሉ። በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብና አማራ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በርካታ ዜጎች ከቀያቸው ለመፈናቀል ተገደዋል። በመንግስት በኩል የተፈናቀሉትን ዜጎች የማቋቋም ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ዋና እንባ ጠባቂው ገልጸዋል። ተቋማቸው የተለያዩ ቡድኖች በማዋቀር በታህሳስ 2012 ዓ.ም በተለያዩ ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን  ለማቋቋም እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ላይ ምልከታ አድርጓል። በዚሁ መሰረት በአማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች በመልሶ ማቋቋም ስራ ላይ በተደረገው ምልከታ አመርቂ የሚባሉ ስራዎች መሰራታቸውን አመልክተዋል። በሶማሌ ክልል ቃሎጂ አንድና ሁለት መጠለያ ጣቢያዎች በተደረገው ምልከታ ግን ችግሮች እንዳሉ ለማየት መቻሉን ገልጸዋል። በመጠለያ ጣቢያዎቹ የሚገኙ ዜጎች በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ በነበረ ግጭት ምክንያት ተፈናቅለው የመጡ እንደሆኑና ቁጥራቸውም ከ70 ሺህ በላይ እንደሆነ ነው ዶክተር እንዳለ ያስረዱት። እነዚህ ተፈናቃዮች የዕለት ደራሽ ምግብ በሚፈለገው ጊዜ እየደረሳቸው እንዳልሆነና ሁለትና ሶስት ወር ዘግይቶ እንደሚደርሳቸው መግለጻቸውን ተናግረዋል። አንዳንድ ተፈናቃዮችም የዕለት ደራሽ ምግቡ በፍትሃዊነት እየደረሳቸው እንዳልሆነ መናገራቸውን ጠቅሰው ተቋሙ ባደረገው ማጣራት የተባለው ችግር መኖሩን ማረጋገጥ አልታቸለም ብለዋል። ተፈናቃዮቹ ወደ ኦሮሚያ ክልል የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸውና ባሉበት የሶማሌ ክልል መኖር እንደሚፈልጉ መግለጻቸውንም ጠቁመዋል። ክልሉ ተፈናቃዮቹ ከነዋሪው ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩ ለማድረግ ማቀዱንና ለዚህም የበጀት ድጋፍ እንደሚፈልግ ከክልሉ የስራ ኃላፊዎች ለመረዳት መቻሉንም ጠቅሰዋል። እንደ ተቋማቸው ምልከታ በቃሎጂ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን የማቋቋም ስራው በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል። የማቋቋም ስራው በቂ ባለመሆኑ ምክንያትም ተፈናቃዮቹ ለማኅበራዊና ስነ-ልቦናዊ ችግሮች መጋለጣቸውን ተናግረዋል። በአጠቃላይ በመጠለያ ጣቢያዎቹ ያለው የማቋቋም ስራ በመንግስት በኩል 'ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠው ለማረጋገጥ ተችሏል' ነው ያሉት ዶክተር እንዳለ። ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ለተፈናቃዮች በቂ የዕለት ደራሽ ምግብ ከማቅረብ አንጻር ችግር እንደሌለበት ገልጸዋል። ሆኖም የዕለት ደራሽ ምግብ በማቅረቡ ሂደት የጸጥታ ችግሮች ድጋፉ እንዲዘገይ እያደረጉ መሆኑንና በሶማሌ ክልል ያለው ችግርም የዚሁ አካል መሆኑን አስረድተዋል። የዕለት ደራሽ ምግቡ በፍትሃዊነት መዳረሱን የሚያረጋግጠው ኮሚሽኑ አይደለም ያሉት አቶ ደበበ የኮሚሽኑ ተግባር ድጋፉን ለተጎጂዎች ማድረስ ብቻ እንደሆነም አክለዋል። ምግቡ በፍትሃዊነት የመድረሱን ጉዳይ የመቆጣጠር ሃላፊነት የክልሉ፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች እንደሆነም ጠቁመዋል። ለተፈናቃዮች የሚያስፈልገው የዕለት ደራሽ ምግብና ሌሎች ድጋፎች በወቅቱ ለተጎጂዎች እንዲደርሱ መንግስት የጸጥታ ችግሮችን የመፍታቱን ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበትም ብለዋል። የሠላም ሚኒስቴር የግጭት ዘላቂ መፍትሄ ስርዓት ትግበራ ዳይሬክተር አቶ ግርማ ቸሩ በቃሎጂ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች የተፈናቀሉ የሶማሌ ተወላጆች እንደሆኑ ገልጸዋል። ከዞኖቹ የተፈናቀሉት ዜጎች ከሶማሌ ክልል በድሬዳዋ ሚሊኒየም ፓርክ አካባቢ ተጠልለው እንደሚገኙም ተናግረዋል። የሠላም ሚኒስቴር በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች የሚፈናቀሉ ዜጎች በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ያስችላል ያለውን የዘላቂ መፍትሔ ኢኒሼቲቭ በጥቅምት 2012 ዓ.ም ይፋ ማድረጉም ይታወሳል። በኢኒሼቲቩ አማካኝነት የሶማሌ ክልል የተፈናቃዮችን ጉዳይ የሚቆጣጠር የልዩ ልዑክ ቡድን ማቋቋሙንና ቡድኑ በዚህ ወር ከሶማሌ ክልል መንግስት ጋር በመሆን ከተፈናቃዮቹ ጋር ውይይት ማድረጉንም ገልጸዋል። የተፈናቃዮቹ ተወካዮች ዜጎቹ ለረጅም ጊዜ በመቆየታቸው መንግስት መፍትሔ ከመስጠት አንጻር በቂ ትኩረት አልሰጠንም፣ አስፈላጊውን ድጋፍም አላደረገም የሚል ሀሳብ እንዳነሱ ገልጸዋል። ሚኒስቴሩና የክልሉ መንግስት ለጉዳዩ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት የተፈናቃዮችን የስም ዝርዝር የማደራጀት ተግባር መከናወኑንና ይህም ቀጣይነት እንዳለው ተናግረዋል። ተፈናቃዮቹ ወደነበሩበት ይመለሱ፣ ሌላ ቦታ ሄደው ይስፈሩ ወይስ ከማህበረሰቡ ጋር ተዋህደው ይኑሩ የሚለው ጉዳይ ጊዜ የሚፈልግ እንደሆነና ትኩረትም እንደተሰጠው አመልክተዋል።   የተፈናቃዮቹ ፍላጎት ግን በመንግስት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል አቶ ግርማ።   በዘላቂ መፍትሔ ኢኒሼቲቭ አስፈላጊው የገንዘብ ድጋፍ ከአጋር ድርጅቶች ከተሰበሰበ በኋላ ለሶማሌ ክልል እንዳለው ተጨባጭ ሁኔታ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።   በአሁኑ ወቅት መንግስት በቃሎጂ የመጠሊያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ዜጎች ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነና በመንግስትና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች አስፈላጊው ድጋፍ እየቀረበ መሆኑንም ገልጸዋል።   በክልሉ መንግስት በኩልም አቅም በፈቀደ መልኩ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።   የልዩ ልዑክ ቡድኑ ባደረገው ምልከታ ተፈናቃዮቹ የውሃ፣ የጤናና የትምህርት አገልግሎቶች እያገኙ መሆናቸውን መመልከት ተችሏል ነው ያሉት።   በአጠቃላይ በሶማሌ ክልልና ሌሎች ቦታዎች የሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎች በዘላቂ መፍትሔ ኢኒሼቲቭና ሌሎች መርሃ ግብሮች በሚሰሩ ሁሉን አቀፍ ስራዎች ምላሽ ያገኛሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም