ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አቤቱታዎችን ሁሉ ተቀብሎ የማስተናገድ ውስንነት አለበት

አዲስ አበባ የካቲት 11/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ሁሉ ተቀብሎ በማስተናገድ ሂደት የአሰራርና የአቅም ውስንነት እንዳለበት ተገለጸ። በአዳማ ከተማ በተካሄደው የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ እንደተገለፀው ተቋሙ የህዝብ አቤቱታዎችን የማስተናገድ የአቅም ውስንነት አለበት። የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የባህርዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የምርመራ ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታደሰ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ለተቋሙ በሚቀርቡ አቤቱታዎች ምላሽ አሰጣጥ ላይ ውስንነቶች አሉ። ከሚቀርቡ አቤቱታዎች መካከል በተቋሙ ስልጣንና ተግባር ስር የማይወድቁ ሆነው የሚገኙ እንዳሉ ሁሉ በተቋሙ ስልጣንና መታየት እያለባቸው ምላሽ ሳያገኙ ቀርተው ሲፈተሹ ግን በተቋሙ ስር መታየት ያለባቸው ሆነው ይገኛሉ ብለዋል። ይህ የሚያመላክተው ደግሞ በአሰራር ሂደቱ ተቋሙ የመፈፀም አቅም ውስንነት መኖሩን እንደሆነ ተናግረዋል። በሚቀርቡ አቤቱታዎች ላይ በትክክል የመመዝገብ፣ የማደራጀትና ለአቤቱታዎቹ የሚሰጠው የመፍትሄ ሀሳብ ጥራት የሚጎድለው እንደሆነም ያሳያል ብለዋል። በዚህም ምክንያት በዜጎች የሚቀርቡ በርካታ አቤቱታዎች በተቋሙ በአግባቡ ምላሽ እየተሰጠባቸው አይደሉም ብለዋል። የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የምርመራ ዳይሬክተር አቶ አበራ ሃይሌ በበኩላቸው ተቋሙ ምን አይነት አቤቱታ ያስተናግዳል? በሚለው ዙሪያ የግንዛቤ ችግር በመኖሩ ሰዎች ወደ ተቋሙ ቅሬታ እንዳያቀርቡ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። በዚህ ዙሪያ ተቋሙ ለህብረተሰቡ የንቅናቄ መድረክ በማዘጋጀት ግንዛቤ መፍጠር ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይኖርበታልም ነው ያሉት። በየክልሉ በሚገኙ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የባለሙያ ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ፣ አቤቱታን በሚፈለገው መልኩ እንዳያስተናገድ ምክንያት እንደሚሆንም ተናግረዋል። የተቋሙ የቅሬታ ቅበላ አቅሙን ለማጎልበትም የባለሙያ አቅምን ማጎልበት ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት እንደሚገባው አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሃይሌ እንዳሉት፣ በተለይ በክልሎች በብዛት የህዝብ አቤቱታ የመቀበል የአቅም ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል። በሀዋሳና በባህርዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በአንፃራዊነት የተሻለ የአቤቱታ አቀራረብ ቢኖርም በጋምቤላና አፋር ክልሎች ያለው ግን በብዛት ክፍተት ይታይበታል ነው ያሉት። በክልሎቹ ያለው የአቤቱታ አቀራረብ ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት፣ ቅሬታዎች በሽምግልና እና በተለያዩ ባህላዊ መንገዶች እየተፈቱ በመሆናቸው መሆኑንም አምልክተዋል። በመሆኑም በቀጣይ በምን አይነት መልኩ ማስተናገድ ይቻላል? በሚለው ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር ይደረግበታል ብለዋል። በቀጣይ የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን የአቤቱታ ቅበላ አቅም ለማሳደግ፣ ስልጠና የመስጠትና አቅምን የመገንባት ስራም እየተከናወነ ነው ብለዋል። የሚቀርቡ አቤቱታዎች በተቋሙ ስልጣን ስር የሚወድቁ ናቸው ወይስ አይደሉም? የሚለውንም ጉዳይ በጥልቀት ይፈተሻል ብለዋል። በአጠቃላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎች የቅበላ አቅምን በተመለከተ ያሉ ክፍተቶችን በዝርዝር ለማወቅ ጥናት እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በ1 ሺህ 599 የቅሬታ ሰነዶች ከ31 ሺህ 400 በላይ ሰዎች ለተቋሙ ቅሬታ ማቅረባቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም