ቀጥታ፡

በወላይታ ዞን በበጀት ዓመቱ 862 ሚሊዮን ብር ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ወደ ስራ ገቡ

ሶዶ፣ የካቲት 11/2012 (ኢዜአ) በወላይታ ዞን በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት 862 ሚሊዮን ብር ያስመዘገቡ 38 ባለሀብቶች ወደ ስራ ገቡ። የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክሌ ቶማ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለሃብቶቹ ወደ ስራ የገቡት በግብርና፣ አገልግሎትና ኢንደስትሪ ዘርፎች ነው። የኢንቨስትመንት መሬት በማዘጋጀት፣ የመንገድ ሌሎችንም የመሰረተ ልማት በመዘርጋታቸው ለባለሀብቱ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል። አካባቢው የተረጋጋ መሆኑ ባለሀብቶችን ለመሳብ ሌላው የተመቻቸ ሁኔታ እንደሆነም ጠቅሰዋል። በዞኑ ማህበረሰብ ዘንድ ያለው የዳበረ የስራ ባህልና በሚፈለገው ልክ የሰው ኃይል መኖሩ በግማሽ የበጀት ዓመቱ 15 ታቅዶ 38 ባለሀብቶች ወደ ስራ እንዲገቡ አስችሏል። "ግብርና፣ ኢንዱስትሪና አገልግሎት ባለሃብቶቹ የተሰማሩባቸው መስኮች ሲሆኑ በገጠርና ከተማ ከይገባኛል ጥያቄ ነጻ የሆነ ከ780 ሄክታር በላይ መሬት ተላልፎላቸዋል" ብለዋል፡፡ ባለሀብቶቹ አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላት መሬት ተረክበው ወደ ስራ እንደገቡ ያመለከቱት ኃላፊው  ለ3 ሺህ 500 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረጋቸውም  ተናግረዋል። በዞኑ ኦፋ ወረዳ ማንቻ ጎጋራ ቀበሌ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ ከ100 ሄክታር በላይ መሬት የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ለማምረት ወደ ተግባር ከገቡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አንዱ "ቬጅ ቦክስ ሆርቲካልቸር ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር" አንዱ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ስራአስኪያጅ ጀርመናዊው ሚስተር ሉትዝ ሃርትስማን በበኩላቸው የዞኑ አስተዳደር በቅርበት ሆኖ መንገድ በመገንባትና ሌሎችንም መገልገያዎች በማመቻቸት ያደረገላቸው ድጋፍ በአጭር ጊዜ ስኬታማ እንደሆኑ ገልጸዋል። "በአሁኑ ሰዓት ከ160 በላይ ነዋሪዎች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ ዕድል ተፈጥሯል"ብለዋል። የአካባቢው ማህበረሰብ የሚያሳየው በጎ ምግባርና ለስራ ያለው ተነሳሽነት በጋራ እንዲሰሩ ያደረጋቸው መሆኑን ጠቅሰው አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞች የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል። ሌላው ባለሀብት አቶ ያዕቅብ አልታዬ እንዳሉት በአባላ አባያ ወረዳ በሃማሳ ወንዝ ዳር ከ50 ሄክታር በላይ መሬት በመረከብ ሙዝ ማምረት ጀምረዋል። በተደረገላቸው ድጋፍ በአጭር ጊዜ ውስስጥ ወደ ስራ መግባት እንደቻሉ ተናግረዋል። ድርጅታቸው በተያዘው ዓመት ብቻ ከ300 ለሚበልጡ የአከባቢው ነዋሪዎች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል በአካባቢው የስራ እድል ተጠቃሚ ከሆኑት ነዋሪዎች መካከል አቶ ካስትሮ ጌታ በሰጡት አስተያየት በተፈጠረላቸው የስራ ዕድል በሚያገኙት ገቢ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። ወጣት ትጋቱ ወታሮ በበኩሉ ባለሀብቶች በፈጠሩት የስራ እድል ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል። አስረኛ ክፍል ትምህርቱን ቢያጠናቅቅም ውጤት ባለማምጣቱ ተስፋ አስቆርጦት እንደነበርና  አሁን ግን ባገኘው የስራ ዕድል ደስተኛ መሆኑን ገልጿል። በቀን በሚያገኘው ገቢ ከራሱ አልፎ ቤተሰቡን እየረዳ እንደሚገኝ ጠቅሶ ከሚያገኘው ገቢ በመቆጠብ ለተሻለ ውጤት እንደሚሰራም ጠቁሟል። በወላይታ ዞን ባለፉት አስር ዓመታት ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት አስመዝግበው ወደስራ የገቡ 494 ባለሀብቶች ከ26 ሺህ 500 በላይ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ ከዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም