መጪውን ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ ለማድረግ ኃላፊነታችንን እንወጣለን--የሲቪክ ማኅበራት - ኢዜአ አማርኛ
መጪውን ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ ለማድረግ ኃላፊነታችንን እንወጣለን--የሲቪክ ማኅበራት
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11/2012 (ኢዜአ) መጪው ምርጫ ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ እንዲሆን የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሲቪክ ማኅበራት ገለጹ።
ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ ሰሞኑን አስታውቋል።
የምርጫው ውጤት ነሐሴ 23 እና 24 ቀን 2012 ዓ.ም በምርጫ ጣቢያ፤ ከነሐሴ 24 እስከ 28 በክልሎች ይፋ እንደሚሆንም የገለጸ ሲሆን የቦርዱ የተረጋገጠ ውጤት ደግሞ ከነሐሴ 24 ቀን እስከ ጳጉሜ 3 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚገለጽ ማስታወቁ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽንና ኮንሰርቲየም ሲቪክ ኤንድ ቮውተር ኢጁኬሽን የተሰኙት የሲቪክ ማኅበራትም ለምርጫው እያደረጉት ስላለው ዝግጅት ገልጸዋል።
ማኅበራቱ ከመራጮች ምዝገባ መርሃ ግብር ጀምሮ በየደረጃው ባሉ ሒደቶች ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የአገሪቷ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና ከምርጫ በኋላ ለመራጩ ሕዝብ ግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮችን ማመቻቸት የሚያስችሉ እቅዶችን ለመተግበር 'እየሰራን ነው' ብለዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ ማኅበራቸው የቀደመ የምርጫ ተሳትፎ ልምዱን በመጠቀምና ከአቻ ማኅበራት ጋር በመሆን በተለይ የምርጫው ሒደት ሠላማዊ እንዲሆን የድርሻውን እንደሚወጣ ነው የገለጹት።
ማኅበሩ ከሌሎች የሲቪክ ማኅበራት ጋር በመጣመር መራጮች በቅድመ ምርጫ ወቅት እንዲመዘገቡ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአግባቡ እንዲለዩና ይጠቅመኛል ላሉትም ድምጻቸውን እንዲሰጡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እንደሚሰራም ጠቅሰዋል።
ለምርጫው ሠላማዊ መሆን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ፖሊሲዎቻቸውን በግልጽ እንዲያስቀምጡ፤ ደጋፊዎቻቸውን በማክበር በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱም ትምህርት እንሰጣለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ስዩም በበኩላቸው መጪው ምርጫ ሠላማዊ እንዲሆን በተለይ ሴቶች ያላቸውን ጉልህ ድርሻ በአግባቡ እንዲወጡ የሚያደርጉ ስራዎች ይከወናሉ ይላሉ።
በዋናነት ሴቶች የምርጫ ካርድ በመውሰድና በመምረጥ፣ በመመረጥና በታዛቢነት እንዲሳተፉ ከማድረግ ባሻገር ለምርጫው በሠላም መጠናቀቅ የሠላም ምክር ቤት መቋቋሙን ገልጸዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች ስለ ስትራቴጂና ፖሊሲዎቻቸው ለመራጯ ሴት ግንዛቤ እንዲፈጥሩ ለማድረግ የጋራ መድረኮች ለመፍጠር እየሰራን ነውም ብለዋል።
ኮንሰርቲየም ሲቪክ ኤንድ ቮውተር ኢጁኬሽን የተሰኘው የሲቪክ ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ሳህለስላሴ አበበም ለምርጫው ስኬት ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ችግሮች ቢከሰቱ በውይይትና በሠላማዊ መንገድ እንዲፈቱ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም የመራጮቻቸውን ድምጽ እንዲያከብሩ ለማድረግ የሚጠበቅብንን የማስተማር ስራ ለመስራት ተዘጋጅተናል ብለዋል።
ከገዥውም ሆነ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ተጽዕኖ ውጭ በመሆንም በቅድመ ምርጫ በማስተማር፣ በምርጫ ወቅት በመታዘብና ከምርጫም በኋላ ያሉ ሒደቶችን ሪፖርት በማድረግ እንሰራለንም ብለዋል።