"መደመር" የህዝቦችን አቅም ወደ ብልፅግና የሚወስድ ሰፊ መንገድ ነው... ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
"መደመር" የህዝቦችን አቅም ወደ ብልፅግና የሚወስድ ሰፊ መንገድ ነው... ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ
አዲስ አበባ የካቲት 11/2012 (ኢዜአ) የመደመር እሳቤ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችን አቅም ወደ ብልፅግና የሚወስድ ሰፊ መንገድ እንጂ ጥቂቶች የሚበለፅጉበት መስመር አይደለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስተሩ በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ ተገኝተው በወራቤ ስታዲየም ለተገኘው የአካባቢው ማህበረሰብ መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም "የመደመር" እሳቤ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችን አቅም ወደ ብልፅግና የሚወስድ ሰፊ መንገድ እንጂ ጥቂቶች የሚበለፅጉበት ጠባብ መስመር አይደለም ብለዋል።
"የኢትዮጵያ ሰላም በዘላቂነት እውን የሚሆነው በጠንካራ የልማት ስራ እንጂ በጦር መሳሪያ አይደለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ የልማት ስራዎች ስኬት ላይ የስልጤ ህዝብ ተጠቃሽ መሆኑንም አንስተዋል።
የስልጤ ህዝብ በተለያዩ የልማት ስራዎች በመሳተፍ የአገር ብልፅግና እውን መሆን እንደሚችል ያሳየ ታታሪ ህዝብ መሆኑንም አውስተዋል።
አሁን ላይ "ለኢትዮጵያ ከድህነት ውጭ ሌላ ከባድ ፈተና የለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በመደመር እሳቤ በትብብር ብልፅግናዋን እውን ለማድረግ ህዝቡ በጋራ እንዲቆም ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰአት በኋላ በሚኖራቸው ቆይታም ከአካባቢው ነዋሪዎች ከተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።