ቀጥታ፡

የዘንድሮ 12ኛ ክፍል ብሄራዊ ተፈታኞች ኦንላይን ይመዘገባሉ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 10/2012(ኢዜአ) ዘንድሮ በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና የኦንላይን ምዝገባ ስርአት በመላው አገሪቱ ተግባራዊ እንደሚደረግ የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ረዲ ሽፋ እንዳሉት በ2010 እና 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በሙከራ ደረጃ ተወስኖ የነበረው የኦንላይን ምዝገባ ስርአት በመላው አገሪቱ ባሉ የፈተና ጣብያዎች ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል።

የኦን ላይን ምዝገባው ካሁን በፊት ከእንግሊዝ ሲመጣ የነበረውን የምዝገባም ሆነ የመልስ መስጫ ወረቀት እንደሚተካ የገለጹት አቶ ረዲ ከሁሉም ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊዎች ጋር  በመነጋገር በትምህርት ቤቶቹ ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱ ጠቁመዋል፡፡

አንዳንድ የግብአትም ሆነ የአቅም ማነስ የሚያጋጥማቸው ጣብያዎች ካሉም በነባሩ አሰራር በወረቀት የመመዝገብ ሂደት ሊተገበር እንደሚችልም ከክልሎች ጋር መግባባት ላይ መድረሳቸውንም ገልጸዋል።

የኦንላይን ምዝገባውን በትክክል ለማስኬድም ባለፈው ወር ለክልል የፈተና ጉዳይ አስፈፃሚና ለአይሲቲ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡

በአዲሱ ፍኖተ ካርታ መሰረት ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባለሙያዎች ሲዘጋጅ የነበረው ፈተና የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ በኩል እንዲዘጋጅ በመወሰኑ  ፈተናውን በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውን  ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ፈተናውን አለም አቀፍ ደረጃው የጠበቀ ለማድረግ በተቋሙ ያሉ ባለሙያዎች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው የፈተናው ዝግጅት ወደ መጠናቀቅ እየተቃረበ  ነው ብለዋል።

የህትመት ስራውን ለመጀመርም የተለያዩ ማተሚያ ቤቶችን ባሳተፈ መልኩ ጨረታ ወጥቷል ያሉት አቶ ረዲ፤ ባለፈው አመት የተከሰተው ችግር ማህበረሰቡ በተቋሙ ላይ የነበረውን እምነት የሸረሸረ እና መጥፎ ትዝታን አስቀምጦ ያለፈ እንደነበረ አንስተዋል፡፡

በ2012 በጀት አመት የሚሰጠው ብሄራዊ ፈተና ባለፉት አመታት ያጋጠሙ ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ በተሻለ ጥንቃቄ ለመስጠት ቅድመ ዝግጅቱ መጠናቀቁም ዳይሬክተሩ ተናግሯል፡፡

ፈተናው ያለምንም ችግር በስኬት እንዲጠናቀቅ የተማሪ፣ ወላጅና ማህበረሰብ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ትምህርት የፖለቲካ ማስፈፀምያ እንዳይሆን እያንዳንዱ ህብረተሰብ አስተዋጽኦውን እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም