ዩኒቨርሲቲዎቹ የዓባይ ወንዝ መረጃዎችን በምርምር መጻሕፍት ሊያሰናዱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲዎቹ የዓባይ ወንዝ መረጃዎችን በምርምር መጻሕፍት ሊያሰናዱ ነው
አዲስ አበባ ሰኔ 20/2010 የአዲስ አበባና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር የታገዙና በታላቁ ዓባይ ወንዝ ላይ ያተኮሩ 12 መጻሕፍት እያዘጋጁ መሆኑ ተገለጸ። ዩኒቨርሲቲዎቹ ከዚሁ ጎን ለጎንም የዓባይ ወንዝ በኢትዮጵያዊያን ባሕል፣ እምነትና ታሪክ ውስጥ ያለውን ሚና በማጥናት ላይ ናቸው። ከሶስት ዓመታት በፊት የተጀመረው ይህ የአባይ ወንዝን ምሉእ ታሪክና ሕዝቦች አኗኗርና መስተጋብር ጋር ያለውን ቁርኝት የማጥናት ሂደት አሁን ላይ የመጻሕፍቱን ቢጋር ማዘጋጀት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ዛሬ በአዲስ አበባ በጋራ በመከሩበት መድረክ ላይ ለማወቅ እንደተቻለው "ዓባይ በኢትዮጵያዊያን ባሕል ውስጥ" በሚል ጥናትና ምርምር እያደረገ ያለው ፕሮጀክት መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማጥናት በመተንተን 12 መጻሕፍትን ለማሳተም እየሰራ መሆኑ የተነገረው። “የዓባይ በኢትዮጵያዊያን ባሕል ውስጥ” ፕሮጀክት ዋና አስተባባሪ ዶክተር አለኸኝ መርሻ እንዳሉት ስራዎቹ ከተለያዩ ምንጮች በርከት ያሉ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማጥናትና በመተንተን መጨረሻ ላይ ለትውልድ የሚተላለፉና ኢትዮጵያዊያንና ቀሪው ዓለም ዓባይ ወንዝን በሚመለከት ትክክለኛ መረጃ እንዲጨብጡ የሚያስችሉ ናቸው። ዓባይ ወንዝ በፖለቲካው በኢኮኖሚው፣ በመልከዓ-ምድራዊ፣ በባሕልና ትውፊት በሙዚቃ፣ በግጥም፣ በትያትር፣ ሀገረሰባዊ እምነት፣ በተረትና እንቆቅልሽ፣ እንዲሁም በእስልምና እና በክርስትና መጻሕፍት ውስጥ የተገለጸበትን መረጃ በመመርመርና በማጥናት 12 ያሕሉ መጻሕፍት በእንግሊዝኛ እና አማርኛ ቋንቋዎች ይዘጋጃሉ ነው ያሉት። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማእከል ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ዘሪሁን ወልዴ በበኩላቸው ዓባይ ብሔራዊ መልክን የሰጠ፤ ከባሕልና እምነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘና ኢትዮጵያን በቀሪው ዓለም እንድትታወቅ ያደረገ ጉልሕ አርማ ነው ይላሉ። ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምሮ ዓባይን በየዘመናቱ በዜማ ሲመርቁት፤ ሲረግሙት፤ በቅኔ ሲያወድሱት፤ ብርእ ቀርጸው፤ ብራና ዳምጠው በሊቃውንት አንደበት ሲያወድሱት እንደኖሩ የሚያስረዱ በርከት ያሉ መረጃዎች መገኘታቸውን ይገልጻሉ። በመሆኑም ዓባይ ካለው ጉልሕ ጠቀሜታ አንጻር ምሁራን ምርምርና ጥናትን መሰረት ያደረጉ መረጃዎችን በመሰብሰብ በወንዙ ላይ የተሻሉ ሐሳቦችን እንዲያፈልቁ፤ አሁን ላይ በጥናት እየተዘጋጁ ያሉ መጻሕፍት ሚናቸው ከፍተኛ ይሆናል ነው ያሉት ፕሮፌሰር ዘሪሁን። ዓባይ ወንዝን በተመለከተ ብዙ መጻሕፍት ይኑሩ እንጂ የተጻፉት በውጪ ሀገራት ሰዎች በመሆኑ የተዛቡና እርግጠኛ መሆን የማይቻልባቸው መረጃዎች አሉ፤ ያሉት ፕሮፌሰር ዘሪሁን ኢትዮጵያዊያን እንቁ ሐብታቸው የሆነው ዓባይን በትክክለኛ መረጃ አውቀው እንዲጠብቁት ያስፈልጋል ብለዋል። በመሆኑም አሁን ላይ በ“ዓባይ በኢትዮጵያዊያን ባሕል ውስጥ ፕሮጀክት” የሚያሳትማቸው የምርምር መጻሕፍት ክፍተቱን የሚሞሉ ናቸው ብለዋል። በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የዓባይ ባሕል ልማት ጥናትና ምርምር ማእከል ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉቀን አንዷለም "ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ዓባይን በትክክል አላጠኑትም" ይላሉ። ዶክተር ሙሉቀን እኛ ኢትዮጵያዊያን ሐብታችንን ባለማወቃችንና መረጃ ባለማስቀመጣችን ምክንያት የውጪ ሀገራት ዜጎች ስለ ዓባይ እርግጠኛ ያልሆኑ መረጃዎችን ሁሉ ጽፈዋል ይላሉ። በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን በሙሾ፣ በቅኔ፣ በመንዙማ፣ በሙዚቃ፣ በእንቆቅልሽ፣ በተረትና በሌሎች ዘርፎች ያስቀመጧቸውን ያልተሰናዱ መረጃዎችን ሰብስቦ ማከማቸት፤ ማጥናትና መተንተን ምሁራን ሁሉ ሊሰሩት የሚገባ ተግባር ነው ብለዋል።