ቀጥታ፡

ከውጭ የሚገቡ መሰረታዊ ፍጆታዎች በአገር ውስጥ ለመተካት እየተሰራ ነው

ሰመራ ኢዜአ የካቲት 9 ቀን 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ ለመሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ከውጭ ለማስገባት በዓመት በአማካይ የምታወጣውን 2 ቢሊዮን ዶላር በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት  እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ ። የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ እንደገለፁት ኢትዮጵያ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ በርካታ ወንዞች ፣ ሰፊ ለም መሬትና ከቆላ እስከ ደጋ ለግብርና ስራ አመቺ የሆነ የአየር ፀባይ ባለቤት ናት ። በህብረተሰቡ ውስጥ ጠንካራ የስራ ባህል አለመፈጠር ፣ የግብርና ስራችን በሚፈለገው ደረጃ ከባህላዊ አሰራር አለመላቀቅና ተገቢውን የቴክኖሎጂ ግብአቶች አለመጠቀም በፍጥነት እያደገ የመጣውን የህዝብ ፍላጎት ማሟላት እንዳልተቻለ ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል ። እምቅ ሃብቱን በአግባቡ ጥቅም ላይ ባለመዋሉ በዓመት በአማካይ በ2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ስንዴ ፣ ሩዝ ፣ ዘይት ፣ ስኳር ፣ ወተትና የወተት ተዋፅኦ የመሳሰሉ መሰረታዊ ምርቶች ከውጭ ለማስገባት ተገድዳለች ። ለቴክኖሎጂ ሽግግር ማገለገል የሚገባውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ መጠን በአገር ውስጥ መመረት ለሚገባቸው የግብርና ውጤቶች መዋሉ አዋጪ አይደለም ያሉት ሚኒሰትር ዴኤታው በሚቀጥሉት አምሰት ዓመታት በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ። ይህንኑ ለማሳካት የቆላ ስንዴን በመስኖ የማልማት ሰፊ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን ለሩዝ ልማት ተስማሚ የሆኑ የአማራ ፣ ደቡብና ጋምቤላ አካባቢዎች ተለይተው የዘር ብዜት ስራ መጀመሩን ገልፀዋል ። የቆላ ስንዴ ልማት በሚካሔድባቸው አካባቢዎች የቅባት ሰብሎችን በማምረት በአገር ውስጥ ፋብሪካዎች በቂ ዘይት ለማምረት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ሚኒስተር ዴኤታው ተናግረዋል ። አቅዱ ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች በአገር ውስጥ ከመተካት ባሻገር ወደ ውጭ በመላክ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ያለመ ነው ብለዋል ። የውጭ ምንዛሪ ወጪውን በማስቀረትና ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ አቅም በመፍጠር መልሶ ግብርናውን የበለጠ ለማዘመንና ከኢንዱሰትሪ ጋር በማስተሳሰር ተወዳዳሪነታችንን ለማጎልበት የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች ለማስገባት እድል ይፈጥራል ተብሏል ። በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶችና ግለሰቦች በቂ ብድርና አስፈላጊ የቴክኖሎጂ አቅርቦት መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ለማሟላት ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ከአቶ ሳኒ ረዲ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተወካይ አቶ ጌታቸው ወቄ በበኩላቸው ግብርናው  እንደ ማኑፋክቸሪንግና እንደ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትልልቅ ህንጻዎችን የሚገነቡበት ባለመሆኑ ከማስያዣ ጋር ተያይዞ ብድር ማግኘት የሚቻልበት እድል እንዳልነበረ ገልፀዋል ። ልማት ባንክ ተንቀሳቃሽ ሃብቶችን ፣ የቤት እንስሳትንና የተዘሩ ሰብሎችን እንደመያዣ በመጠቀም በግብርናው ሴክተር ለሚሰማሩ ባለሃብቶችም ሆነ ገበሬዎች ብድር ለመስጠት የሚያስችለው አሰራር መዘርጋቱን አስረድተዋል ። የሰብል ልማትም ሆነ የእንስሳት ሃብትን ለማዘመን ለሚፈልጉ አካላት በቂ የብድር አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም