ሰባተኛው አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት በዚህ ሣምንት ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት በዚህ ሣምንት ይካሄዳል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 9/2012 ሰባተኛው አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት በመጪው ሐሙስ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት አስታወቀ፡፡ ሽልማቱ ''ጥራት የላቀ አገራዊ አጀንዳ እንዲሆን እንሰራለን!'' በሚል መሪ ቃል የሚካሄደውን ሽልማት አስመልክቶ የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ስድስት ተቋማትና ድርጅቶች ይሸለማሉ። በፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት በሚካሄደው መርሐ ግብር በሰባት ዘርፎች ዓለም አቀፍ የጥራት መለኪያዎችን መሠረት ያደረገ ሽልማትና እውቅና እንደሚሰጥ ተገልጿል። በሽልማቱ ለትርፍ የተቋቋሙና ያልተቋቋሙ 25 አምራች ድርጅቶችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንደተወዳደሩም ተመልክቷል። የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ''ኢትዮጵያ በምርቶች ጥራት በዓለም ያላትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ጥራት ያላቸው ምርቶችን ለማውጣት ለሽልማቱ መወዳደር ያስፈልጋል'' ብለዋል። ዓለም አቀፍ የጥራት መስፈርቶችን መሠረት ዕውቅና ለማግኘት የሚወዳደሩ ተቋማት ቁጥር መጨመር እንዳለበትም ተናግረዋል። የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ መብራቱ ኢትዮጵያ ጥራት ባላቸው ምርቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ክፍተቶችን መሙላት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ''የጥራት ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው። በጥራት ማምረት ካልተቻለ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ መወዳዳር ስለማይቻል ዶላር ማምጣት አይቻልም። ይህን ማድረግ ካልተቻለ አገር መለወጥ አይቻልም'' ብለዋል። ጥራት ላይ የማይደራደር ኅብረተሰብ መፈጠር እንዳለበት ያመለከቱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ መንግሥት የምርት ጥራትን ለማስጠበቅ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ድርጅቱ ባለፉት 11 ዓመታት 349 ድርጅቶችና ተቋማትን አወዳድሮ 66ቱን መሸለሙን አስታውቋል። ድርጅቱ በዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መቋቋሙ ይታወሳል፡፡