ለኢትዮጵያ ህዳሴ መረጋገጥ የድርሻችንን እንወጣለን--የካሜሩንና የጋና ባህላዊ አስተዳደር መሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ ህዳሴ መረጋገጥ የድርሻችንን እንወጣለን--የካሜሩንና የጋና ባህላዊ አስተዳደር መሪዎች
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 9/2012 ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ትታወቅበት ወደ ነበረው ስልጣኔና ገናናነት እንድትመለስ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝና የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑ የካሜሩንና የጋና ባህላዊ አስተዳደር መሪዎች ገለጹ። የባህላዊ አስተዳደር መሪዎቹ ሰሞኑን በአዲስ አበባ በነበራቸው ጉባኤ የአህጉሩን ችግር ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እንደሚሰሩ መግለጻቸው ይታወቃል። የባህላዊ አስተዳደር መሪዎቹ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በአፍሪካ በቅኝ ግዛት ስር ወድቀው የነበሩ አገሮች ነጻነታቸውን እንዲያገኙ ኢትዮጵያ የጎላ አስተዋጽኦ አበርክታለች። 'ይህንን የኢትዮጵያ ውለታ አፍሪካውያን የሚረሱት አይደለም'' ብለዋል። የካሜሮን ባህላዊ ንጉስ ዶክተር ሮቢንሰን ታኒዬ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ወደነበረችበት ታላቅነት መመለስ አለባት። በአውሮፓ ካሉ አየር መንገዶች ጋር ተወዳዳሪ እንደሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁሉ በሌሎችም ዘርፍ ኢትዮጵያ ነጥራ እንድትወጣ የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ትልቁ የአቪዬሽን ኢንደስትሪ ተቆጣጣሪ አየር መንገድ አንደሆነ ሁሉ በባህልና በሌሎችም መስኮች ጎልታ እንድትታይ እንደ አንድ የባህል መሪ የበኩሌን አደርጋለው ብለዋል። እንደ ንጉስ ዶክተር ሮቢንሰን ታኒዬ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በቅኝ አለመገዛቷ ባህሏን ጠብቃ ለማቆየት ያስቻላት በመሆኑ ይህ የዳበረ ባህል ለአገር እድገት መዋል አለበት። ''በዚህ ረገድ ህዝባችንን ተጠቃሚ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራት አለብን'' ብለዋል። "ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን ህዝቦች ነጻነት ዋጋ የከፈለች አገር ናት" የሚሉት ደግሞ የጋና ባህላዊ መሪ ናና አዩሜዱ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ መድመቂያ ቀለም እንደሆነች ተናግረዋል። ለአፍሪካ አገሮች የነጻነት ትግል የኢትዮጵያ አሻራ የጎላ መሆኑንም አስታውሰዋል። በመሆኑም በትምህርትም፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በግብርናና በስራ እድል ፈጠራ በትብብር ለመስራት ዝግጁ እንደሆኑ ናና አዩሜዱ አመልክተዋል። አዲስ አበባ ውስጥ በተካሔደው የአፍሪካ ባህላዊ አስተዳደር መሪዎች መድረክ የኮትዲቫር፣ የካሜሮንና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የባህል መሪዎችን ጨምሮ ሌሎችም እንግዶች ታድመውበታል። መድረኩ በቀጣይ አምስት አመት እቅድ ላይ ውይይት አድርጎ "የአፍሪካ ባህላዊ መሪዎች ጉባኤ" ለማቋቋም ከሶስት ወራት በኋላ ቀጠሮ ይዞ ተለያይቷል።