የኢትዮጵያ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚያቀርባቸው እርምጃዎች እየተተገበሩ አይደለም - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚያቀርባቸው እርምጃዎች እየተተገበሩ አይደለም

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚያቀርባቸው የእርምት እርምጃዎች በታችኛውና መካከለኛው የመንግስት አስተዳደር እርከን ተገቢውን ምላሽ እንደማያገኙ ተገለጸ። ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆየው የተቋሙ የስድስት ወር የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው። የኢትዮጵያ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 1142/2011 መሰረት የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት ስራ ላይ ማዋል እንዲችል ማንኛውም ሰው አስፈላጊውን ድጋፍ የመስጠትና የመተግበር ግዴታ ይደነግጋል። ተባባሪ የማይሆኑ የመንግስት ባለስልጣናት ተጠያቂነት እንዳለባቸውና ማንኛውም ሰው ያለበቂ ምክንያት በተቋሙ በቀረበ የምርምራ ውጤትና መፍትሄ ወይም ቁጥጥር ውጤት መሰረት በ 30 ቀናት ውሰጥ የእርምት እርምጃ መውሰድ ይገባል። ይህ ሳይሆን የቀረ እንደሆነ ከ5 እስከ 7 ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም በ 10 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ወይም በሁለቱም በገንዘብና በእስራት እንደሚቀጣ በአዋጁ ተቀምጧል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሀይሌ እንዳሉት፤ በተቋሙ የተሰጡ የመፍትሄ ሃሳቦችን ተግባራዊ ያላደረጉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ ነው። ይሁን እንጂ በታችኛውና በመካከለኛው የመንግስት አስተዳደር እርከን ላይ የሚገኙ ተቋማት በቀረቡላቸው የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ተገቢ ምላሽ የሰጡ አለመሆኑን ገልጸዋል። የተሰጠውን ውሳኔ ባልፈፀሙ አካላት ላይ ተቋሙ በአዋጅ በተሰጠው የመክሰስ መብት በሀድያ ዞን ሶሮ ወረዳ አስተዳደርና ጊምቢቹ ከተማ መዘጋጃ ቤት ሁለት የስራ ሃላፊዎች በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወንጀል ክስ መስርቶ እያንዳንዳቸው በአምስት ሺህ ብር እንዲቀጡ መደረጋቸውን ጠቁመዋል። ''የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ የቀረበለትን የመፍትሄ ሃሳብ ባለመፈፀሙ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዲጋለጥ አድርገናል'' ብለዋል። በባህር ዳር በሁለት የክስ መዝገቦች ክስ እንዲመሰረት ለፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ቀርቦ አያስከስስም ተብሎ መዝገቡ መዘጋቱን ገልጸዋል። በአጠቃላይ በዝቅተኛና መካከለኛው የመንግስት አስተዳደር እርከኖች ላይ ያሉ አስፈጻሚ ተቋማት የቀረቡ የመፍትሄ ሃሳቦችን ከማስፈጸም አንጻር የአመራሮች ቁርጠኝነት ክፍተት እንዳለ መለየቱን ጠቁመዋል። በፌዴራል ተቋማት ላይ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚያቀርባቸው የመፍትሄ ሃሳቦችን ተቀብሎ የእርምት ርምጃ ከመውሰድ አንጻር ከጊዜ ወደጊዜ መሻሻል ቢታይም ለጉዳዩ በቂ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አመለልክተዋል።