በባህር ዳር ከተማ ዘጠነኛው የናይል ማራቶን የሩጫ ውድድር ዛሬ ተካሔደ - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳር ከተማ ዘጠነኛው የናይል ማራቶን የሩጫ ውድድር ዛሬ ተካሔደ
ባህርዳር፣ የካቲት 8/2012 (ኢዜአ) መነሻውንና መድረሻውን ባህርዳር መስቀል አደባባይ ያደረገው ዘጠነኛው የናይል ማራቶን የሩጫ ውድድር ዛሬ ተካሔደ። የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር መሀሪ ታደሰ በውድድሩ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ከተማዋ ዓለም አቀፍ የሩጫ ውድድሮች እንዲካሄዱባት እንሰራለን ብለዋል። በየዓመቱ በሚካሄደው የናይል ማራቶን ሩጫ በዓለም ታዋቂ የሆኑ አትሌቶች የሚሳተፉበት መድረክ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልፀዋል። ይህም ወጣቱ አካላዊ ብቃቱ የጠነከረ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ ከተማዋ ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ለማሳደግ ያግዛል። የናይል ማራቶን አዘጋጅና ዋና ስራአስኪያጅ አትሌት መልካሙ ተገኝ በበኩሉ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ለ8 ተከታታይ ዓመታት የባህርዳር ከተማ የጎዳና ሩጫ በሚል ስያሜ ሲካሄድ ቆይቷል። የባህርዳር ከተማ ሩጫን ደረጃ በማሳደግ ሀገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ አትሌቶች እንዲሳተፉ ለማድረግ ሲባል ዘንድሮ ወደ ናይል ማራቶን እንዲያድግ መደረጉን ተናግሯል። በዓለም አደባባይ የምናውቃቸውን አትሌቶች በቀጣይ በናይል ማራቶን በመጋበዝ የአባይ መነሻ የሆነችውን የባህርዳር ከተማን ገፅታ ለመገንባትና የቱሪስት መናኽሪያ ለማድረግ መታቀዱን አስረድቷል። እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮችን በስፖርቱ የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከርና አትሌቲክስ ስፖርትን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን አስረድቷል። በ9ኛው የናይል ማራቶን የሩጫ ውድድር በኦሎምፒክና በዓለም ሻምፒዮና ደረጃ የሚሳተፉ አትሌቶች የሚኒ ማሟያ ውድድር እንዲሆን ለማድረግ ታስቦ እየተሰራ እንደሆነም ገልጿል። ዘንድሮ በ10 ኪሎ ሜትር የተጀመረው የናይል ማራቶን በቀጣይ ወደ ግማሽ ማራቶንና ወደ ሙሉ ማራቶን ውድድር በማሳደግ ዓለም አቀፍ አትሌቶችን ጨምሮ ከ40 ሺህ በላይ ተወዳዳሪዎች እንዲሳተፉ ይደረጋል። ከኢትዮጵያ ሆቴል አትሌቲክስ ክለብ በውድድሩ አንደኛ የወጣችው አንችንአሉ ደሴ በበኩሏ በውድድሩ አሸናፊ መሆኗ በቀጣይ የሀገሯን ስም ለማስጠራት እንድትበረታ መነቃቃት ፈጥሮላታል። በወንዶች የአዲስ አበባው መብራት ሃይል አትሌቲክስ ክለብ በመወከል በውድድሩ የተሳተፈው አትሌት ጊዜው አበጀ በበኩሉ ባለፈው ዓመት በባህርዳር ከተማ ሩጫ ተሳትፎ 3ኛ በመሆን አጠናቆ እንደ ነበር አስታውሶ ዘንድሮ በናይል ማራቶን 1ኛ በመውጣቱ መደሰቱን ገልጿል የናይል ማራቶን ሩጫንም በሱዳን የገዳሪፍ ግዛት ፖሊስ ኮሚሽነር ሜጀር ጄኔራል አብደላ ሀሰንን ጨምሮ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት፣ የክልሉና የከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች በጋራ ውድድሩን አስጀምረዋል በውድድሩም በሁለቱ ፆታዎች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ለወጡ አትሌቶች የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በዘንድሮው የናይል ማራቶን የሩጫ ውድድር ከ5ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ተሳታፊ ሆነዋል።