ቀጥታ፡

የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ አባል ሆነ

አርባ ምንጭ፣ የካቲት 8/2012 (ኢዜአ) የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ጋዴፓ/የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ አባል መሆኑን ይፋ አደረገ፡፡ የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ጋዴፓ/የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ ግንባር አባል መሆኑን ይፋ ያደረገው ትናንት በአርባ ምንጭ ከተማ ባካሔደው አንደኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ ነው። የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ጋዴፓ/ በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ መሰረት ህዳር 26 ቀን 2012 ዓ.ም ክልላዊ ፓርቲ ሆኖ ህጋዊ ሰውነት አግኝቶ እየሠራ እንደሚገኝ በጉባኤው ተገልጿል። የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ዳሮት ጉምአ ለጉባዔው እንደተናገሩት ፓርቲያቸው በዓላማ ተቀራራቢነት ካላቸው ፓርቲዎች ጋር በህግ በተፈቀዱ አሠራሮች ተባብሮ በመስራት ድርጅታዊ አገልግሎቱን ለማስፋት ሲሠራ ቆይቷል። በዚሁ መሰረት የጋዴፓ አመራሮች ከመድረክ አመራሮች ጋር በመወያየት በጋራ ተባብሮ ለመስራት ከስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል። የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጋዴፓ በይፋ ኦፌኮ፣ ኢሶዴፓ፣ ሲአን፣ ወህዴግና አህደፓ አካትቶ ከያዘው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ ጋር መቀላቀሉን የፓርቲው ሊቀመንበር ተናግረዋል። የጋዴፓ ጠቅላላ ጉባኤ  አባላት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ ከፓርቲያቸው ጋር ባለው የርእዮተ ዓለም  ተቀራራቢነትና አንድነት ላይ በስፋት በመወያየት አባልነቱን በሙሉ ድምጽ አፅድቀውታል። ፓርቲው በ11 ወራት ውስጥ ያከናወናቸው ስራዎች ሪፖርት  ለጉባኤው ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። ትናንት ለአንድ ቀን በተካሔደው የጋዴፓ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን ከሚገኙ 14 ወረዳዎችና 4 ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ አባላትና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም