ሳልቫኪርና ሬክ ማቻር የተኩስ አቁም ስምምነት አደረጉ

አዲስ አበባ ሰኔ 20/2010 የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪርና ዋነኛው የተቀዋሚ መሪ ዶክተር ሬክ ማቻር የተኩስ አቁም ስምምነት አደረጉ። በመጪዎቹ 72 ሠዓታት ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ የሚሆነው ይኸው ስምምነት በሱዳን ርዕሰ መዲና ካርቱም በሁለቱ ተቀናቃኞች መካከል ነው ዛሬ የተፈረመው። ስምምነቱ የደቡብ ሱዳንን የእርስ በእርስ ጦርነት በመግታት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት አስተዋፅኦው የጎላ እንደሚሆን ግምት ተሰጥቶታል። የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አል ዲርዲሪ መሃመድ አህመድ ለአልጀዚራ እንደተናገሩት፤ ሳልቫ ኪርና ሬክ ማቻር የተኩስ አቁም ለማድረግ የሚያስችላቸውን ስምምነት የፈረሙት የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር በተገኙበት ነው። ከዚህ ቀደም በሁለቱ ጎራዎች መካከል የተደረሱት የተኩስ አቁም ሰምምነቶች በተደጋጋሚ መጣሳቸውን ዘገባው አመላክቷል። ይሁንና  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሀገሪቱ ላይ ሊጥል የነበረውን ማዕቀብ ከግምት አስገብተው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት አገራት መሪዎቹ እርቅ እንዲያወርዱ ግፊት ማድረጋቸውም ተጠቁሟል። በደቡብ ሱዳን ባለፉት አምስት ዓመታት በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ግጭት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ለስደት ተዳርጓል። ከዚህም ሌላ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ከቀዬው ተፈናቅሏል፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል። በአሁኑ ወቅት ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑ ደቡብ ሱዳናዊያን ደግሞ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ጠቅላላ የህዝብ ብዛቷ 12 ሚሊዮን እንደሚሆን የሚገመተው ደቡብ ሱዳን አዲስ ሀገር ሆና የተመዘገበች እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2011 ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም