ሃገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና የባህል ፌስቲቫል በደብረ ማርቆስ ከተማ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ሃገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና የባህል ፌስቲቫል በደብረ ማርቆስ ከተማ ተጀመረ
ደብረ ማርቆስ ኢዜአ የካቲት 7/ 2012 ፡- 17ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና 13ኛው የኢትዮጵያ የባህል ፌስቲቫል ዛሬ በደብረ ማርቆስ ከተማ ተጀመረ። በመክፈቻው ስነሰርዓት ወቅት የኢፌዴሪ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ሰለሞን አሰፋ እንዳሉት የባህል ስፖርት ውድድሮች በመካባበር ላይ የተመሰረተ አንድነትን ለማጠናከር አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። የማንነት መገለጫ የሆኑ ባህሎች በመጤው እንዳይበረዙ በተለይ ወጣቱ የአካበቢው ብሎም የሀገሩ ባህልና ወግ መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል። "በዚሁ ውድድር እና ፌስቲቫልም ስፖርተኞች ከውድድርና ፉክክር ባለፈ ባህላቸውንና ልምዳቸውን እርስ በርስ የሚለዋወጡበት መድረክ ነው "ብለዋል። ውድድሩ በ13 የባህላዊ ስፖርቶች ዓይነት የሚከናወን ሲሆን ከእነዚህም ገና ፣ ትግል፣ ፈረስ ጉግስ፣ ሽርጥ፣ ገበጣና ቀስት ውርወራ ይገኙበታል። የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ይትባረክ አወቀ በበኩላቸው ውድድሩ የአካባቢው የባህል ስፖርት እንዲነቃቃ ብሎም ከተማዋን የበለጠ ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝ ተናግረዋል። የከተማው ማህበረሰብ በተለይም ወጣቱ ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት መልኩ የመጡ ስፖርተኞችን ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ገልፀዋል። ከተጫዋቾች መካከል የትግራይ ክልልን ወክሎ የተገኘው ወጣት መብራቱ ገብረህይወት እንዳለው በገና ጨዋታ ክልሉን ወክሎ መገኘቱን ተናግሯል። በደብረማርቆስ ከተማ የተደረገላቸው የእንግዳ አቀባበልም በማህበራዊ ትስስር ድህረ ገጽ ከሚመለከተው በተገላቢጦሽ እንደሆነ አመልክቷል። "ስፖርት ፍቅርና አንድነትን የሚሰብክ መድረክ ነው" ያለው ወጣቱ እርሱም አንድነትንና ዘላቂ ሰላምን በሚያመጡ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚሰራ ገልጿል። "ፊላ" የተባለ የባህል ጭዋታ ለማሳየት መምጣቱን የተናገረው ደግሞ ከደቡብ ክልል የመጣው ኩታየ ጌታሁን ነው። "ውድድሩ አሸናፊ ለመሆን ከመጣር ባለፈም እርስ በእርስ ለመተዋወቅና በቀጣይ ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ያግዛል "ብልል። በውድድሩ ትግራይ፣ አማራ፣ ቤንሻልጉል ጉምዝ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ክልሎች እንዲሁም የድሬድዋ የአዲስ አባበ ከተማ አስተዳደሮች ለመሳተፍ ተዘጋጅተዋል። "የባህል ስፖርት ለሀገራዊ አንድነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ ከየካቲት 7 እስከ 15/2012 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን ከ700 በላይ ስፖርተኞችና የልኡካን ቡድን አባላት ተገኝተዋል።