ቀጥታ፡

ሙገር ሲሚንቶ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን በማሸነፍ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ሆኗል

አዲስ አበባ ( ኢዜአ) የካቲት 7/2012 በሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ሙገር ሲሚንቶ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን በማሸነፍ የሊጉ መሪ ሆኗል። የአምናው የሊጉ አሸናፊ ወላይታ ድቻ መከላከያን አሸንፏል። የሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ከሶስት ሳምንታት እረፍት በኋላ ዛሬ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ተጀምሯል። የሶስት ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ሙገር ሲሚንቶ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን 3 ለ 0 በማሸነፍ ነጥቡን ወደ 20 በማሳደግ የሊጉን መሪነት ከመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ተረክቧል። በሌላ ጨዋታ የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ወላይታ ድቻ መከላከያን 3 ለ 0 በመርታት ነጥቡን ወደ 19 ከፍ አድርጎ ከነበረብት ሶስተኛ ደረጃ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል። የፕሪሚየር ሊጉ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነገ ይካሄዳሉ። ሮቤ ላይ ከጠዋቱ 3 ሰአት ጣና ባህርዳርን የሚያስተናግደው መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ውድድሩን ካሸነፈ ወደ ሊጉ መሪነት ይመለሳል። በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰአት ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር ይጫወታሉ። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ በክልል ከተሞች የተካሄዱ ሲሆን ከምባታ ዱራሜ የአምናውን የሊጉ አሸናፊ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማን አስተናግዶ 30 ለ 26 አሸንፏል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ከምባታ ዱራሜ ነጥቡን ወደ 10 ከፍ በማድረግ ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ጋር በነጥብ እኩል የሆነ ሲሆን በግብ ክፍያ ተበልጦ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በቦንጋ መምህራን ኮሌጅ ሜዳ በተደረገው ሌላኛው ጨዋታ መከላከያ ሚዛን አማንን 29 ለ 21 አሸንፏል። የፕሪሚየር ሊጉ ቀሪ መርሃ ግብሮች ነገ ቀጥለው ይካሄዳሉ። መቐለ ላይ ከጠዋቱ 3 ሰአት በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው መቐለ ሰብዓ እንደርታ የሊጉን መሪ ቂርቆስ ክፍለ ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ የሚጠበቅ ነው። በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከጠዋቱ 2 ሰአት ከ30 ፌዴራል ፖሊስ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች  ይጫወታሉ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም