ቀጥታ፡

የ700 አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የካይዘን አመራር ከ3 ቢሊዮን ብር አድኗል

አዳማ ኢዜአ የካቲት 07/2012፡- የካይዘን አመራርና አሰራር ፍልስፍናን በ700 አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ተግባራዊ በማድረግ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን መቻሉን የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ የካይዘን አሰራርና የአመራር ፍልስፍና ተግባራዊ በማድረግ ጥሩ አፈፃፀምና የተሻላ ተሞክሮ ካላቸው ተቋማት ጋር በቢሾፍቱ ከተማ ለሁለት ቀናት መክሯል።

በዚህ ወቅት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረመስቀል ጫላ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት  የካይዘን ፍልስፍ ጊዜና ወጪን በቆጠበ መልኩ ውጤታማና ተደራሽ  ማድረግ  ነው።

በዚህም የአገልግሎት ጥራትና ምርታማነት ለማምጣት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

እስካሁንም 700  በሚሆኑ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመጀመሪያ ዙሪ የካይዘን ትግበራ ውጤታማ በመሆን ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳኑን መቻሉን አስታውቀዋል።

እነዚህን ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ የካይዘን ትግበራ ማስገባት ቀጣዩ ስራቸው መሆኑን አውስተዋል።

በተጨማሪም ተቋማት የራሳቸውን ችግር በራሳቸው አቅም እንዲፈቱ የሚያስችል የካይዘን የልህቀት ማዕከል ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ መሆኑንም አስታውቀዋል።

"አሰራሩ በዋናነት የሰው አመለካከትና አስተሳሰብ መለወጥ ነው "ያሉት አቶ ገብረመስቀል፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ኮሌጆች፣ መካክለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ሌሎች የልማት ድርጅቶች እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በካይዘን ፍልስፍና ትግበራ ውጤታማ ተብለው በምክክር መድረኩ ከተሳተፉት ተቋማት መካከል የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ  አንዱ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ካይዘንን ተግባራዊ በማድረግ በአገልግሎትና በመማር ማስተማር ላይ ውጤታማ መሆኑን  የዩኒቨርሲቲው የለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ መኩሪያ አስናቀ ገልጸዋል።

በተማሪዎች የምግብ አገልግሎት አሰጣጥ፣ በእንስሳት ምርምርና በመማር ማስተማር ላይ የካይዘን ሥራ አመራርና የአሰራር ፍልስፍና ተግባራዊ የሆኑባቸው የሥራ ክፍሎች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

የጥቁር አባይ ትራንስፖርት አክስዮን ማህበር ተወካይ አቶ እድገት ጎበዜም በበኩላቸው "የካይዘን የሥራ አመራርን ተግባራዊ በማድረግ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን ችለናል "ብለዋል።

በተለይም የፈጠራ ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ከ48 በላይ የፈጠራ ሥራ በማከናወንና የድርጅቱን ችግር በራስ አቅም በመፍታት በካይዘን ትግበራ ውጤታማነት በሀገር ደረጃ  የወርቅና የብር ሜዳለያ  መሸለማቸውን  ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም