ሰራዊቱ የሃገር ሰላምና ደህንነትን የማስጠበቅ ተልእኮውን በትጋት ይወጣል..የምስራቅ እዝ ዋና አዛዥ

105
ኢዜአ የካቲት 7/2012 የመከላከያ ሰራዊት የሃገርን ሰላምና የህዝቦችን ደህንነት የማስጠበቅ ተልዕኮውን በትጋት እንደሚወጣ የምስራቅ እዝ ዋና አዛዠ ሜጄር ጀነራል ዘውዱ በላይ ተናገሩ። የምስራቅ ዕዝ ስምንተኛውን የመከላከያ ሰራዊት ቀን በጽዳት ዘመቻ፣በደም ልገሳና በፓናል ውይይት አክብሯል። በሀረር ከተማ በሚገኘው የመኮንኖች ክበብ በተዘጋጀው የፓናል ውይይቱ ላይ ዋና አዘዡ እንደተናገሩት ሰራዊቱ የሚያጋጥሙትን ችግሮች በማለፍ በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። "በተለይ በቀጠናው የሚያጋጥሙ የጸጥታ ችግሮችን ለመከላከል ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በትዕግስትና በጥንቃቄ እየሰራ ይገኛልም" ብለዋል። "በተለይም በህዝብ ላይ የሚቃጡ የአካልና የንብረት ጥቃቶችን ህግን መሰረት ባደረገ መልኩ የመከላከል ሃላፊነታችንን በቁርጠኝነት እንወጣለን" ብለዋል። የአካባቢው የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም የእርቅና የማግባባት ስራን በማጠናከር በህዝብ መካከል የነበረውን ማህበራዊ ትስስርና ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል። በፓናል ውይይቱ ላይ "ሰራዊታችን ለድል ያበቁት ህዝባዊ ባህርያቶችና ቁልፍ እሴቶቹ በተቋማዊ ለውጥ ትግበራ" የሚል ጽሁፍ ያቀረቡት በዕዙ የ13ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጀነራል አሊጋዝ ገብረ እንዳመለከቱት ለህግ የበላይነትና ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ሰራዊቱ በበለጠ ጥንካሬ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል። "በአካባቢው የሚገኙ አመራርና የጸጥታ አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ በመፍታት የተጀመረውን ለውጥ በጋራ ማስቀጠል ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል። በፓናል ውይይቱ ላይ ከሐረሪ ክልል የተገኙት የማህበረሰብ ተወካይ አቶ ዱላ ሚኖጂ "ሰራዊቱ  በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን ትዕግስት በተሞላበት መልኩ የሚያከናውነው ስራ ውጤት እያመጣ ይገኛል" ብለዋል። ይህንም ለማጠናከር በአካባቢያቸው አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ችግሮች ሳይባባሱ በፍጥነት እልባት ለመስጠት የእርቅና ሽምግልና ኮሚቴ በማዋቀር የበኩላቸውን ስራ እያከናወኑ መሆናቸውንና በሌሎችም አካባቢዎች ተሞክሮውን እያስፋፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በክልሉ የጸጥታ መደፍረስ በሚከሰትበት ወቅት ሰራዊቱ መስዋትነት በመክፈል አካባቢውን ወደ ቀድሞው ሁኔታ በመመለስ ህዝቡ ተረጋግቶ እንዲኖር እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ አፈወርቅ ደመቀ ናቸው። ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የመከላከያ ሰራዊቱ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የሚያደርገው ጥረት እንዲሳካ እሳቸውን ጨምሮ ሁሉም የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግረዋል። በእለቱም የአገልግሎት ጊዜያቸውን መሰረት በማድረግ ከምክትል አስር አለቃነት እስከ ኮሎኔልነት ማዕረግ የደረሰ ሹመት ለአባላት ተሰጥቷል። በፕሮግራሙ የምስራቅ ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ፣የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የጸጥታ አካላት ኃላፊዎች ፣ የህብረተሰብ ተወካዮች፣ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም