ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በመካከለኛው ምስራቅ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ( ኢዜአ) የካቲት 7/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በመካከለኛው ምስራቅ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱ ላይ ኑሯቸውን በመጠለያ ያደረጉ 53 ኢትዮጵያዊያን ችግረኛ ሴቶች ተገኝተዋል። ኑሯቸውን በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ያደረጉ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ተወካዮችና በከፍተኛ የኢኮኖሚ ስኬት ላይ የሚገኙ ሴቶችም በውይይቱ ተሳትፈዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋርም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የሠላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልና የገቢዎች ሚኒስትሯ አዳነች አቤቤ በመድረኩ ተገኝተዋል። ኢትዮጵያዊያኑ ሴቶች አሉብን ያሏቸውን ችግሮች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በምላሻቸው መንግስት በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ደህንነት ለማሻሻል 'ቀን ከሌት እየሰራ ነው' ብለዋል። በተባበሩት ዓርብ ኤሚሬቶች ቆይታቸውም ይህን ጉዳይ በአብይ አጀንዳነት እንደሰሩበት ነው የገለጹት። "በገንዘብ እጥረት ምክንያት ወደ አገራችሁ መመለስ ያልቻላችሁ ካላችሁ ከእኔ ጋር ወደ ኢትዮጵያ መሄድ ትችላላችሁ" ሲሉም ለተሳታፊዎቹ ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬ ውሏቸው ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች ጋር በጉዳዩ ላይ እንደሚወያዩም ነግረዋቸዋል። በአካባቢው የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ሚሲዮኖች የዜጎችን ጉዳይ ቀዳሚ አድርገው እንዲንቀሳቀሱም በሁነቱ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም