የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ነገና ከነገ በስቲያ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ነገና ከነገ በስቲያ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀመራል
አዲስ አበባ ጥር 6/2012(ኢዜአ) የሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በሮቤ ከተሞች በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀመራል። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ነገና ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ። ጥር 17 ቀን 2012 ዓ.ም የመጀመሪያው ዙር የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ከተጠናቀቀ በኋላ ክለቦች ለሦስት ሳምንት እረፍት አድርገው ቆይተዋል። ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ30 ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከሙገር ሲሚንቶ፤ ከረፋዱ 4 ሰዓት መከላከያ ከወላይታ ዲቻ ይጫወታሉ። ከነገ በስቲያ ሮቤ ላይ ከጠዋቱ 3 ሰዓት የፕሪሚየር ሊጉ መሪ መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጣና ባህርዳርን ያስተናግዳል። እሁድ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ከቀኑ 9 ሰዓት ይጫወታሉ። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ እና ሙገር ሲሚንቶ በተመሳሳይ 17 ነጥብ በግብ ልዩነት ተበላልጠው በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ የአምናው የሊጉ አሸናፊ ወላይታ ድቻ በ16 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ጣና ባህርዳር ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን ስምንት ደረጃ ይዟል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በክልል ከተሞች በአዲስ አበባ ይካሄዳሉ። ነገ ከረፋዱ 5 ሰዓት ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜ ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ፤ በቦንጋ መምህራን ኮሌጅ ሜዳ አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ክለብ ሚዛን አማን ከተማ ከመከላከያ ጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። ከነገ በስቲያ ከጠዋቱ 3 ሰዓት በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው መቐለ ሰብዓ እንደርታ የሊጉን መሪ ቂርቆስ ክፍለ ከተማን በሜዳው ያስተናግዳል። እሁድ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ፌዴራል ፖሊስ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። ጎንደር ከተማና ቡታጅራ ከተማ በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ጨዋታ የማያደርጉና በእረፍት የሚያሳልፉ ክለቦች ናቸው። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቂርቆስ ከፍለ ከተማና መቐለ ሰብዓ እንደርታ በተመሳሳይ 12 ነጥብ በግብ ልዩነት ተበላልጠው በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ10 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሚዛን አማን ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን 10ኛ ደረጃ ይዟል።