ቀጥታ፡

በአዳማ ከተማ የሰላም ሩጫ ተካሄደ

አዳማ፣ የካቲት 06/2012(ኢዜአ ) "ለአዳማ ከተማ አስተማማኝ ሰላም መስፈን እንሩጥ " በሚል መሪ ሀሳብ በከተማው የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የሩጫ ውድድር ዛሬ ተካሄደ። በውድድሩ አንደኛ በመውጣት ተሸላሚ የሆኑት ኮንስታብል በቀለ ጃለታ በሰጡት አስተያየት የከተማዋን ሰላም አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ  የድርሻቸውን እንደሚወጠ ተናግረዋል። አዳማ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተካባብረው በፍቅር የሚኖሩባት የሰላም ተምሳሌት ከተማ መሆኑዋን አውስተው ይህንን ለማጠናከር እንደሚደግፉ አመልክተዋል። "አዳማ በክልሉም ሆነ በሀገር ደረጃ ካሉት ከተሞች በሰላም ተምሳሌትነት የሚትታወቅ ናት "ያለው ደግሞ በባጃጅ ትራንስፖርት የተሰማራው ወጣት አውግቸው በቀለ ነው። ከተማዋ ሁሉም ተከባብረው በሰላም አብሮ የኖሩባትና ወደፊትም እንዲሁ እንድትቀጥል ፍላጎቱ መሆኑን ተናግሯል። "የከተማዋን ገፅታ ለማበላሸት የሚጥሩ ነቅተን በመከታተል የአካባቢያችንና የክልሉን ብሎም የሀገር ሰላም ማስጠበቅ አለብን "ብለዋል። "እኛ የለሊት የባጀጅ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲንሰጥ ለገንዘብ ብቻ ሳይሆን የከተማችንና የአካባቢዋን ሰላም በመጠበቅ ጭምር ነው" ሲል ገልጿል። በሩጫው የተሳተፈው ለከተማዋ ብሎም ለሀገሪቱ ሰላም መሮጥ አለብን በሚል እንደሆነ ጠቅሶ በውድድሩ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳለያ ማግኘቱን አመልክቷል። የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ሙሐመድ ጎዮ በበኩላቸው አዳማ ለሌሎች የክልሉ ከተሞች የሰላምና መቻቻል ምሳሌ መሆኑዋን ጠቅሰው ይህን አኩሪ እሴት ለማጠልሸት የሚጥሩ አካለትን ለማስወገድ ቁርጠኛ ነን ብለዋል። አዳማ ሁሉንም የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች በፍቅር አቅፋ የያዘች መሆኑዋን ጠቅሰው አፍራሽ ተልዕኮ ለማምከን የከተማዋ ህብረተሰብ እንደ በፊቱ በትብብርና በአንድነት መቆም እንዳለበትም አስገዝበዋል። በሩጫ ውድድሩ  የአዳማ ከተማ የፀጥታ ኃይል፣ ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ፣ የባጃጅ ሾፌሮች ጨምሮ የተለያዩ  የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም