በአፍሪካ እስካሁን በኮሮና ቫይረስ የተጠቃ ሰው የለም - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ እስካሁን በኮሮና ቫይረስ የተጠቃ ሰው የለም
አዲስ አበባ፣ 6/2012 (ኢዜአ) በአፍሪካ በኮሮና ቫይረስ የተጠቃ ሰው እስካሁን አለመኖሩን የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል አስታወቀ። ማዕከሉ ዛሬ ቫይረሱን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት እስከ ትናንት ድረስ ከ63 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ሰዎች የሚገኙትም በቻይና ነው። ይሁን እንጂ መካከለኛው ምስራቅ፣ አሜሪካ፣ አውሮፓና ኦሽኒያ በሽታው ከታየባቸው አህጉራት መካከል ናቸው። እስካሁን 1 ሺህ 400 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ለህልፈት ሲዳረጉ፣ ከሰባት ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ማገገማቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ኬንጋሶንግ በሰጡት መግለጫ በአህጉሪቷ እስካሁን በበሽታው የተያዘ ሰው የለም። ሆኖም 51 ሰዎች ምልክት ታይቶባቸው ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን ሁሉም ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ተረጋግጧል ብለዋል። የኀብረቱ አባል አገራትና የዓለም ጤና ድርጅትን ያቀፈ ግብረ ኃይል መቋቋሙን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ግብረ ኃይሉ የአባል አገራቱን ዝግጁነት መገምገሙን አስታውቀዋል። ግብረ ኃይሉ በአገራቱ መግቢያዎች ላይ ቁጥጥርና ምርመራ፣ ኢንፌክሽን መከላከልና የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ ድጋፍ መስጠት፣ የላቦራቶሪ ምርመራ እንዲሁም የአደጋ ጊዜ ግንኙነትና የማኅበረሰብ ተሳትፎ ጉዳዮችን እያስተባበረ መሆኑን ጠቁመዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ማዕከሉ ከአባል አገራት ጋር በየቀኑ መረጃ ይለዋወጣል፣ ከአገራቱ ብሔራዊ የኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች ተወካዮች ጋርም የቪዲዮ ኮንፍረንስ ያካሂዳል። ማዕከሉ የኀብረቱ አባል አገራት ቫይረሱን በመካላከሉ ረገድ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ቁሳቁስ ከማሰራጨት ባለፈ፤ ለላቦራቶሪ ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ መሆኑንም አብራርተዋል። እስካሁን ከ16 አገራት ለተውጣጡ ባለሙያዎች ከሴኔጋል መንግሥት ጋር በመተባበር ስልጠና ተሰጥቷል ነው ያሉት። በአሁኑ ወቅትም በኬንያ ተመሳሳይ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ ያስረዱት። ከሚቀጥለው ሣምንት ጀምሮም የላቦራቶሪ ምርመራ፣ የአደጋ ወቅት መረጃ ልውውጥ፣ ክሊኒካል ማኔጅመንትና የኢንፌክሽን መከላከልና ቁጥጥር ስልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል። "ማዕከሉ አባል አገራት በአውሮፕላን ማረፊያዎቻቸው የሚያደርጉት የቫይረስ ልየታ ምርመራ እንዲሻሻል ድጋፍ እያደረገ ነው" ብለዋል። ለምርመራው የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን በማፈላለግ ለአባል አገሮች እያከፋፈለ መሆኑንም አክለዋል።