ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያግዝ ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ተከፈተ

አዲስ አበባ ጥር 6/2012  የኢትዮጵያን የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልምድና ተሞክሮ ለማስፋትና የዘርፉን ተሳትፎዋን ለማሳደግ ይረዳል የተባለ ኤግዚቢሽን ዛሬ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል። ኤግዚቢሽኑ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አገራትና የሕንድ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልምድና ተሞክሮን ለመቅሰም ያስችላታል ተብሏል። የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከሕንድ ዓለም አቀፍ የጨርቃጨርቅና ማሽነሪ ኤግዜቢሽን ማኅበር ጋር ያዘጋጁት ዓለምአቀፍ የጨርቃጨርቅ ማሽነሪና ምህንድስና ኤግዚቢሽን ለሶስት ቀናት ይቆያል። "አይ.ቲ.ኤም.ኢ አፍሪካ 2020" በተሰኘው ኤግዚቢሽን የአፍሪካ አገራትን ጨምሮ 10 የዓለም አገራት የተሳተፉበት ሲሆን ከ170 በላይ ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎቶቻቸውን አቅርበውበታል። የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው እንደገለጹት ኢትዮጵያ ካላት የጥጥ ሀብትና ነባራዊ ሁኔታ አኳያ በዘርፉ እምብዛም አልተጠቀመችበትም። ሌሎች የአፍሪካ አገራትም ባላቸው የሰው ሃይል፣ ሰፊ የእርሻ መሬትና ምቹ የአየር ሁኔታ ያልተሰራበትን ይህን ዘርፍ ማሳደግ የሚችሉበት ትልቅ ዕድል መኖሩን ጠቁመዋል። በመሆኑም በዘርፉ ትልቅ ተሞክሮ ካላቸው እንደ ሕንድ ካሉ አገራት ተሞክሮዎችን፣ ልምዶችና ለኢንዱስትሪው የሚጠቀሙትን ማሽነሪዎች ማወቅ በዘርፉ ለመስራት ትልቅ ጥቅም አለው ብለዋል። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረእየሱስም ኤግዚቢሽኑ ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ አገራት በዘርፉ ያሉበትን፤ ሌሎች ደግሞ የደረሱበትን ቴክኖሎጂ ለመፈተሽ ይረዳል ብለዋል። ኢትዮጵያ ከኤዥያና ከአውሮፓ አገራት በብዛት የምታስገባቸውን የጨርቃጨርቅ ምርቶች በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት ዘርፉን ማዘመን ላይ ትኩረት ሊደረግ ስለሚገባ እንዲህ ያሉ የእውቀት ሽግግሮችን ማምጣት ያሻል ነው ያሉት። የሕንድ አይ.ቲ.ኤም.ኤ ማኅበር ሊቀመንበር ሚስተር ሃሪ ሻርከር የኤግዚቢሽኑ ዓላማ ማኅበሩ በሕንድ ከ40 ዓመታት በላይ የዘለቀ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ተሞክሮውን በአፍሪካ በማስተዋወቅ በአገራቱ መካከል የንግድ ትስስርና የኢኮኖሚ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሆነ ገልጸዋል። በአገር ውስጥ የሚገኙ በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ማኅበራትና በየክልሉ ያሉ የዘርፉ ተወካዮች ኤግዚቢሽኑን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል። በኤግዚቢሽኑ ከአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ጋና፣ ቦትስዋና፣ ኬንያና ሌሎችም አገራት ተሳትፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም