ቀጥታ፡

በሰሜን ወሎ ዞን በኤች አይቪ/ኤድስ መከላከል ላይ የአስተሳሰብ ስርጸት ለማምጣት እየተሰራ ነው

ወልዲያ፣ የካቲት6/2012( ኢዜአ ) በኤች አይቪ/ኤድስ መከላከል ላይ የአስተሳሰብ ስርጸት ለማምጣት እየሰሩ መሆናቸውን በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኙ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸውና ሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ። በማህበረሰብ ጥምረት ኮሚቴ 2 ነጥብ7 ሚሊየን ብር በመሰብሰብ ተጋላጭ ለሆኑ ወገኖች ድጋፍ መደረጉ የመከላከል ስራውን አጠናክሮ ለማስቀጠል  ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ ገልጿል። በወልዲያ ከተማ የሚገኘው የተስፋ ብርሃን ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሞላ ገበያው በሰጡት አስተያየት ማህበሩ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸውን 600 ወገኖችን በማቀፍ ህብረተሰቡን በማስተማር ላይ አተኩሮ እየሰራ ነው። እርሳቸውን ጨምሮ የማህበሩ አባላት በትምህርት ቤቶች፣ በእምነት ተቋማት፣ በስፖርታዊ ውድድሮችና ሌሎች ህዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ትምህርት በመስጠት የሚስተዋለውን መዘናጋት ለማስቀረት እየሰሩ ነው። ከማህበረሰብ ጥምረት የሚያገኙትን ድጋፍ ለእያንዳንዱ አባል በየወሩ ከ300 ብር በላይ በመስጠት በማስተማር ስራቸው ላይ እንዲያተኩሩ እገዛ እየደረገ ይገኛል። "በወልድያ ሆስፒታል ለህክምና የሚመጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ስለኤች አይ ቪ ኤድስ/ መተላለፊና መከላከያ መንገዶች ዘወትር እያስተማርኩ ነው" ያሉት ደግሞ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩት ወይዘሮ ገነት ሲሳይ ናቸው። ለማስታመም የሚመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በማተኮር ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁና ቫይረሱ የሚገኝባቸውን ግለሰቦችም ከጭንቀትና ከተስፋ መቁረጥ እንዲወጡ እያገዙ ይገኛሉ። ወጣት አገር ሰጠኝ በበኩሏ ቤዛ በተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት ድጋፍ ከነበረችበት ሴተኛ አዳሪነት ወጥታ በድርጅቱ ጊቢ የምግብ፣ የሻወር አገልግሎትና የልብስ፣ የሳሙናና ሌሎች ድጋፎችን ማግኘቷን ገልጻለች። በቡና ቤቶች በመዘዋወር ሴተኛ አዳሪዎች በኮንዶም አጠቃቀምና ሌሎች ኤች አይ ቪ ኤድስን መከላከያ መንገዶችን በማስተማር ለገንዘብ ሲሉ ራሳቸውን ማጋለጥ እንደሌለባቸው ትመክራለች። በሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ የኤች አይ ቪ ኤድስ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ባለሙያ አቶ ኢዮብ ሰፊው በሰጡት አስተያየት ኤችአይቪ/ኤድስን በመከላከል ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል። ቀደም ሲል በማህበር ተደራጅተው የነበሩ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖች የውጭ ድጋፍ ከመቀነሱ ጋር ተያይዞ ተበትነው እንደነበር ጠቁመው የበሽታው ስርጭትም በአንጻሩ እየጨመረ መጥቶ እንደነበር አውስተዋል። በግማሽ ዓመቱ  2ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በማህበረሰብ ጥምረት በማሰባሰብ ሁለት ሺህ ለሚሆኑ ወገኖች ድጋፍ በማድረግ ተቀዛቅዞ የነበረው የማስተማር ስራ እንደገና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተደርጓል። ይህም ከ58 ሺህ 880 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ ማገዙን ጠቁመው ቫይረሱ በደማቸው የተገኘባቸው 519 ሰዎች ህክምና እንዲከታተሉ ተደርጓል። ድጋፉም "የአገራችን ህዝቦች ለዘመናት የዘለቀውን የእርስ በእርስ መደጋገፍና መረዳዳት ባህል ይበልጥ ከማጎልበት ባሻገር ህብረተሰቡ የባህሪ ለውጥ እንዲያመጣ የሚያስችል ነው" ሲሉ ገልጸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም