ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፍሪካ የመጀመሪያው የንግድ ኢክስፖ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ያቀረቡት ሀሳብ ተቀባይነት አገኘ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአፍሪካ የመጀመሪያው የንግድ ኢክስፖ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ያቀረቡት ሀሳብ በአፍሪካ አገራት ተቀባይነት ማግኘቱን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ነቢያት ጌታቸው ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዛሬ ለአገር ውስጥና ለውጭ መገናኛ ብዙሃን መገናኛ ባለሙያዎች መግለጫ ሰጥተዋል። በቅርቡ በአዲስ አበባ ተካሄዶ በነበረው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የተገኙ ውጤቶችና የተላለፉ ውሳኔዎችንም አብራርተዋል። የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ምስረታን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአፍሪካ የመጀመሪያው የንግድ ኤክስፖ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ያቀረቡት ሀሳብ በኅብረቱ አገራት ተቀባይነት ማግኘቱን ገልፀዋል። የንግድ ኤክስፖው በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ሀሳቡ ተቀባይነት ማግኘቱን እንጂ መቼ ይካሄዳል በሚለው ጉዳይ ላይ ቃል አቀባዩ አስተያየት አልሰጡም። “ከስብሰባው ጎን ለጎን በተካሄዱ የጎንዮሽ መድረኮች የጤና፣ የአጀንዳ 2063፣ የባህልና የቅርስ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈው የኢትዮጵያን ጥቅም ከማስጠበቅ ባሻገር ለአፍሪካ ብልጽግና ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነት ማሳየት ችለዋል” ብለዋል። የአገሪቷን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ በሕብረቱ ጉባኤ ላይ ውሳኔዎች እንዲተላለፉ መደረጉንም ነው የተናገሩት። የሁለትዮሽ ውይይትን በተመለከተም ከናይጄሪያ፣ ከኖርዌ፣ ከኢኳቶሪያል ጊኒ እና ከካናዳ መሪዎች ጋር ውጤታማ ምክክር መደረጉን አቶ ነቢያት አንስተዋል። በሌላ የቃል አቀባዩ ማብራሪያ በቻይና እየተማሩ ካሉ ኢትዮጵያዊያን እስካሁን በኮሮና ሻይረስ የተጠቃ እንድም ሰው አለመኖሩን አስታውቀዋል። ተማሪዎቹ በኮሮና ቫይረስ እንዳይጠቁ አስፈላጊው ክትትል እየተደረገላቸው ስለመሆኑም ተናግረዋል። በቻይና የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በግላቸውና በመንግስት ነፃ የትምህርት ዕድል ተሰጥቷቸው የሚማሩ ተማሪዎች በቫይረሱ እንዳይጠቁ ቻይና የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ክትትል እያደረገ ሰለመሆኑም ገልጸዋል። “ኢትዮጵያዊያኑ ተማሪዎች ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ችግር እንዳልገጠማቸው ተረጋግጧል“ ብለዋል። እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ የቫይረሱ መነሻ በሆነችው ሁቤ ግዛት ውሃን ከተማ ከ300 በላይ ኢትዮጵያዊያን ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ። መንግስት ለተማሪዎቹ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ በወሰነው መሰረት ቤጂንግ ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲና የተማሪዎቹ ማኅበር በአፈፃፀሙ ላይ በጋራ እየሰሩ ሰለመሆኑም ጠቁመዋል። በሌላ በኩል በታንዛንያ ዳሬሠላም በተለያዩ እስር ቤቶች የነበሩ 128 ኢትዮጵያዊያን ዛሬ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱም ቃል አቀባዩ ጨምረው ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም