ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ብሔራዊ ጥቅሟን የማያስጠብቅ ስምምነት አትፈርምም

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ከየትኛውም አካል በሚደረግ ተጽዕኖ ብሔራዊ ጥቅሟን ያላስጠበቀ ስምምነት እንደማትፈርም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ነቢያት ጌታቸው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል። ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ በዋሽንግተን ዲሲ ሲያደርጉት የነበረው ድርድርና ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ዝግጅት ሳይቋጭ መጠናቀቁ ይታወቃል። በቃል አቀባዩ መግለጫ ይህንኑ አስመልክቶ ከጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል። በድርድሩ ሱዳን የአቋም ለውጥ አድርጋ ከግብጽ ጋር መወገኗ፣ አሜሪካና የዓለም ባንክም ለግብጽ መወገናቸው አሁን ላይ ጉዳዩን "4 ለ 1" አድርጎታል፤ በዚህም ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና እየተደረገ ነው፣ እዚህ ላይ የኢትዮጵያ አቋም ምንድነው ተብለው ተጠይቀዋል። ቃል አቀባዩ በምላሻቸው በግድቡ ዙሪያ ከየትኛውም አካል ተጽዕኖ ቢኖር ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ እንደማትሰጥና በመርህ ላይ የተመሰረተና ጥቅሟን ያስጠበቀ ድርድር እንደምታራምድ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ እንደማትሰጥም በአጽንኦት ተናግረዋል። በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ በተመለከተ ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ለማዘጋጀት በዋሽንግተን ዲሲ ሲካሄድ የነበረው ውይይት በዚህኛውም ዙር ሳይቋጭ ትናንት ማማምሻውን መጠናቀቁ ይታወሳል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም