ቀጥታ፡

በሁከት ምክንያት የተጠቁ 746 ሺህ ህጻናት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ ዕቅድ ይፋ ሆነ

የካቲት 6/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በተከሰተ ሁከት ምክንያት የተጠቁ 746 ሺህ ህጻናት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ ውጥን ይፋ ተደረገ፡፡ መርሃ ግብሩ በ“ኤዱኬሽን ካን ኖት ዌይት” በሚባል ድርጅት ይፋ የተደረገ ሲሆን በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በ44 ወረዳዎች የሚተገበር ይሆናልም ተብሏል፡፡ በትምህርት ሚኒስቴር የበላይነት ለሚመራው ለዚህ መርሃ ግብር 165 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተመድቦለታል፡፡ በዕቅዱ ይፋ ማድረጊያ ስነ-ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የ“ኤዱኬሽን ካን ኖት ዌይት” ዳይሮክተር ያስሚን ሸሪፍ፤ “መርሃ ግብሩ በጥቃት፣ በድርቅ፣ በመፈናቀልና በሌሎች ሁከቶች የተጎዱ ህጻናትን ተጠቃሚ ያደርጋል” ብለዋል፡፡ በመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ከሚሆኑ 746 ሺህ ህጻናት ውስጥ 365 ሺህ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ለመርሃ ግብሩ ከተያዘው በጀት 27 ሚሊዮን ዶላሩ የተለቀቀ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ቀሪው 138 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በጀት በሶስት የትግበራ ዓመታት ውስጥ የሚለቀቀ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጺዮን ተክሉ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠሩ ሁከቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ህጻናት የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ “መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገርም የተለያዩ የተራድኦ ድርጅቶች በሚያደርጉት ድጋፍ ጥራት ያለውን ትምህርት ለተጠቁ ህጻናት ለማድረስ ያስችላል” ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ 728 ትምህርት ቤቶች በግጭትና በተፈጥሮ አደጋዎች የተነሣ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑም በስነ-ስርዓቱ ላይ ተመልክቷል፡፡ “ኤዱኬሽን ካን ኖት ዌይት” የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት በትጥቅ ግጭት፣ ድንገተኛ አደጋዎችና በአስገዳጅ መፈናቀሎች በተጠቁ 30 አገሮች ውስጥ ተመሳሳይ ተግባር ማከናወኑ ተጠቁሟል፡፡            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም