ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2019 የግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ ሽልማት አሸናፊ ሆነ

የካቲት 6/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2019 የግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ ሽልማትን ለመጀመሪያ ጊዜ በ"ምርጥ የንግድ ባንክ" ዘርፍ ማሸነፉ ተገለጸ። ባንኩ በተጠናቀቀው 2019 የአውሮፓዊያን ዓመት በተለያዩ ዘርፎች ከተወዳደሩ የተለያዩ አገራት ባንኮች መካከል "ምርጥ የንግድ ባንክ" በሚለው ምድብ ነው ማሸነፍ የቻለው። የዋንጫና የመስክር ወረቀት ሽልማቱን ያበረከተው ግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ የተሰኘ የምርምር፣ የህትመትና የሽልማት ተቋም ነው። የባንኩ ፕሬዚዳንትና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ባጫ ጊና እንዳሉት ባንኩን አሸናፊ ያደረገው ትርፋማ እየሆነ መምጣቱ፣ ተደራሽነቱን እያሳደገ መሄዱ፣ ባሉት የደንበኞቹ ቁጥር ብዛት፣ ለልማት ሥራዎች የሚውል የፋይናንስ አቅርቦት በማሳደጉ፣ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣቱና በሌሎችም አገልግሎቶቹ ነው። ባንኩ ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ምርጥ ባንኮች ደረጃ አግኝቶ እንደነበር አስታውሰው ለዚህ ዓለም አቀፍ ሽልማት ሲበቃ የመጀመሪያው መሆኑን ገልጸዋል፡። እንደ አቶ ባጫ ገለጻ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዘርፈ ብዙ አገራዊ ልማቶችን በፋይናንስ በመደገፍ የበኩሉን እየተወጣ ነው። "በተለይ የአገሪቷ ኢኮኖሚ በጽኑ መሰረት ላይ የተገነባ እንዲሆን የሚያስችሉ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን እየደገፈ ይገኛል" ብለዋል። ለዚህም በኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦትን ለማሳደግ በሚያስችሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ በጋራ ቤቶች ልማት ፕሮግራምና ለግብርና ግብዓቶች የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ የመሰረተ ልማት ሥራዎች እንዲከናወኑ ሲያደርግ መቆየቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል። ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣትም በየዓመቱ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ለሕብረተሰቡ በተለይም በትምህርት፣ በጤናና በአካባቢ ጥበቃ የልማት ሥራዎችን አከናውኗል። በተጨማሪም አካል ጉዳተኞች፣ አረጋዊያን እንዲሁም ሴቶችና ሕጻናትን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረጉ ጥረቶች የበኩሉን እገዛ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። "ያከናወናቸው እነዚህና መሰል ተግባራት ባንኩን ዓለም አቀፍ ሽልማት እንዲቀዳጅ አድርጎታል" ያሉት አቶ ባጫ፣ ሽልማቱ ባንኩ በቀጣይ የሚሰጠውን አገልግሎት እንዲያሳድግና ለሌላ ሽልማት እንዲነሳሳ የሚያደርገው መሆኑን አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ23 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉት ሲሆን፣ በመላ አገሪቷ ከ62 ሺህ በላይ ሠራተኞችና ከ1 ሺህ 560 በላይ ቅርንጫፎች አሉት። ባንኩ በምርጥ ንግድ ባንክነት አሸናፊ በሆነበት የ2019 የግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ ሽልማት ከአፍጋኒስታን፣ ከአርመን፣ ከቦትስዋና፣ ከባህሬንና ከግብጽ የተውጣጡ ባንኮች በተለያዩ ዘርፎች በአሸናፊዎች ዝርዝር ውስጥ መካተታቸው ታውቋል። ከዚህ ቀደምም በካናዳ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ፖርቹጋል፣ ሕንድ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ የሚገኙ ባንኮች የግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ ሽልማት አሸናፊ ከነበሩት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ሽልማቱ ግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ በሚያወጣቸው መስፈርቶች ተመስርቶ የሚካሄድ ነው። ግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ የምርምር፣ የህትመትና የሽልማት ተቋም በባንክ፣ በኢንሹራንስና መሰል የንግድ እንቅስቃሴዎች በተለያዩ መስፈርቶች ውጤታማ የሆኑ ተቋማትን በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናና ሽልማት የሚሰጥ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም