ቀጥታ፡

ከ14ኛው ሳምንት የሊጉ ውድድሮች የቅዱስ ጊዮርጊስና ፋሲል ከነማ ጨዋታ ይጠበቃል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 6/2012 በ14ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ፋሲል ከነማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ የሚጠበቅ ነው። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የ14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ደርሷል። ጨዋታዎቹ በመርሃ-ግብራቸው መሰረት ከነገ ቅዳሜ እስከ ሰኞ ባሉት ቀናት በተከታታይ በክልልና በአዲስ አበባ ይካሄዳሉ። ነገ ከቀኑ በ9:00 ሠዓት መቐለ ሰብአ እንደርታ ከሃዋሳ ከተማ በመቐለ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ይጫወታሉ። ወላይታ ድቻ ከባህርዳር ከተማ፣ አዳማ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ስሁል ሽረ ከሃዲያ ሆሳዕና፣ ጅማ አባ ጅፋር ከድሬዳዋ ከተማ እንዲሁም ፋሲል ከነማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ እሁድ በተመሳሳይ ከቀኑ 9:00 ሰዓት የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው። ፋሲል ከነማና ቅዱስ ጊዮርጊስ በጎንደር ፋሲለደስ ስታዲየም የሚያደርጉት ግጥሚያ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ነው። ሁለቱ ክለቦች ካላቸው የነጥብና የደረጃ መቀራረብ መሪነትን ለማስቀጠል ወይም ለማስረከብ የሚደረግ ፍልሚያ መሆኑ ተጠባቂ እንዲሆን አድርጎታል። ሰኞ ወልቂጤ ከተማ ከሲዳማ ቡና የሚጫወት ሲሆን ሰበታ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና በዚሁ ቀን ከቀኑ በ10:00 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ። በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ26 ነጥብ ሲመራ፣ ፋሲል ከነማ በ25 ነጥብ ይከተላል፤ መቐለ ሰብአ እንደርታ በ22 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። ስሁል ሽረና ባህርዳር ከተማ በእኩል 20 ነጥብ እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ በ19 ነጥብ ከ4ኛ እስከ 6ኛ ባለው ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ኢትዮጵያ ቡና፣ ድሬዳዋ ከተማና ሀዲያ ሆሳዕና ከ14 እስከ 16ኛ ደረጃን በመያዝ በሊጉ ግርጌ ተቀምጠዋል። የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም በ13 ጎሎች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ሲመራ አዲስ ግደይ ከሲዳማ ቡና በ8 ጎል ሁለተኛ፤ ፍጹም አለሙ ከባህርዳር ከተማና ብሩክ በየነ ከሀዋሳ ከተማ ደግሞ በእኩል 7 ጎሎች በሶስተኛ ደረጃ ይከተላሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም