በሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የኮሮና ቫይረስን አስቀድሞ ለመከላከል ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የኮሮና ቫይረስን አስቀድሞ ለመከላከል ዝግጅት ተደርጓል
ሀዋሳ (ኢዜአ) የካቲት 6/2012 የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የኮሮና ቫይረስን አስቀድሞ ለመከላከል ከውጪ ሀገር የሚመጡ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ከበሽታው ነጻ መሆናቸው እስኪታወቅ ድረስ ክትትል የሚደረግበት ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያ ማቋቋሙን አስታወቀ። የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍፁም ከተማ እንደገለፁት ፓርኩ ቻይናውያንና ሌሎች የውጭ ሀገራት ዜጎች ጨምሮ በርካታ የሰው ሀይል ያለበት በመሆኑ የኮሮና ቫይረስን አስመልክቶ አስፈላጊው የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል ። ከኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጤና ኢንስትቲዩት፣ ከደቡብ ክልል ጤና ቢሮ፣ ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የቅድመ ጥንቃቄ ስራው መጀመሩን አስረድተዋል ። የፓርኩ ማህበረሰብ በቫይረሱ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም እያስተማረ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። በተለያዩ መንገዶች ከውጭ ሀገር ወደ ሀዋሳ የሚመጡ ሰዎች ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን የማቆያ ጣቢያ መዘጋጀቱን የተናገሩት አቶ ፍፁም በዚህም ምርመራና ክትትል እየተደረገላቸው እስከ 14 ቀናት እንደሚቆዩ አቶ ፍፁም አስረድተዋል። በደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ እንዳሻው ሽብሩ በበኩላቸው በሀዋሳ በተቋቋመው ጊዜያዊ ማቆያ ውስጥ 14 ቻይናውያን እንደሚገኙ ገልፀዋል። እስከ አሁንም ምንም አይነት ምልክት እንዳልታየባቸው አቶ እንዳሻው ገልፀው በ14 ቀናት ቆይታቸው የተለየ ምልክት ካልታየ ወደ ስራቸው እንዲገቡ ይደረጋል ። ምናልባት ምልክት የሚታይ ከሆነም ተለይተው የሚታከሙበትን ማቆያ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር እየተዘጋጀ መሆኑንና አስፈላጊው ቁሳቁስ መቅረቡን ገልጸዋል። ህክምና የሚሰጡና ክትትል የሚያደርጉ ባለሙያዎችም ሥልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል ብለዋል። እንደ አቶ እንዳሻው ገለፃ ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ጋር ተያይዞ ሀዋሳ ላይ ልዩ ትኩረት የተደረገ ቢሆንም ሌሎች አየር ማረፊያ ባሉባቸው አርባ ምንጭና ጂንካ ከተሞች ላይም ባለሙያዎችን በመላክ የክትትልና የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛል።