በሀዋሳ የሰው ህይወት በማጥፋት ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተያዙ

86
ሀዋሳ ሰኔ 20/2010 በሀዋሳ ከተማ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ወቅት በአሰቃቂ ሁኔታ የሰው ህይወት አጥፍተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የታክቲክ ምርመራ ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር አዲሴ አወኖ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ ድርጊቱን መፈጸማቸውን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ ከተሰራጨው መረጃ ጋር ተመሳሳይነት እንዳላቸው ተመልክቷል፡፡ በዚህም ጥርጣሬ ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው፡፡ በመረጃው  መሰረት ግለሰቦቹ  ከቤት ቃጠሎና ከዝርፊያ ባለፈ ጭካኔ የተሞላበት አሰቃቂ የግድያ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡ ከተጠርጣሪዎች መካከል አንደኛው ግለሰብ አድኑኝ እያለ በሚጮህ ወጣት ላይ የጭካኔ ድብደባ የፈጸመ ሲሆን ሌላኛዋ ደግሞ በተጎጂዎች ላይ እሳት ስትለኩስ የታየውንና በማህበራዊ ሚዲያ የተለቀቀውን ምስል መነሻ በማድረግ መያዟን አስረድተዋል። ምክትል ኮማንደር አዲሴ እንዳሉት  የታያዙት እነዚህ ግለሰቦች " ከኛ ጋር ነበሩ"  ያሏቸውን ግብረ አበሮቻቸውም ፖሊስ በመከታተል በቁጥጥር ስር እያዋለ መሆኑን ገልጸዋል። ፖሊስ በማህበራዊ ሚዲያ  የተለቀቀውን ተንቀሳቃሽ ምስል እንደጠቋሚ መረጃ በመጠቀም ተጠርጣሪ ግለሰቦቹ ሊያዙ እንደቻሉ ጠቁመዋል፡፡ " ከህብረተሰቡና ከፖሊስ እይታ ውጭ የሚሆን ወንጀልና ወንጀለኛ አይኖርም " ያሉት ምክትል ኮማንደሩ ህገ ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል  ህብረተሰቡ እንደወትሮው ሁሉ ወደፊትም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም