ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የቤተሰብ ዕቅድ ፌዴሬሽን በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ እያገኘች ነው

አዲስ አበባ የካቲት 6/2020 (ኢዜአ)ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የቤተሰብ ዕቅድ ፌዴሬሽን አባል ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ ወደ አንድ ሚሊዮን ዶላር ገደማ የፋይናንስ ድጋፍ እያገኘች መሆኗ ተገለጸ። የዓለም አቀፉ የቤተሰብ ዕቅድ ፌዴሬሽን /አይ.ፒ.ፒ.ኤፍ/ የአፍሪካ ዳይሬክተር ሚስ ማሪ-ኢቭሊን ፔትሩስ-ባሪ የአፍሪካን የቤተሰብ ዕቅድ እንቅስቃሴ የተመለከተ መግለጫ ትናንት ምሽት ሰጥተዋል። ዳይሬክተሯ ፌዴሬሽኑ በአፍሪካ ዜጎች የጤና አገልግሎት የማግኘት መብታቸውን ለማሻሻል በአህጉር አቀፍና በብሔራዊ ደረጃ ያስቀመጧቸውን ግቦች እንዲያሳኩ እየሰራ ነው ብለዋል። በአፍሪካ ዕድሜያቸው ከ10 እስከ 24 ዓመት የሆኑ ዜጎች 65 በመቶውን ድርሻ እንደሚይዙ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከፍተኛ ድርሻ ያለው ወጣት አህጉሩን እንዲጠቅምና ፍሬያማ ተግባር እንዲያከናውንም ጤናማ ህይወት እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል። ወጣቱን ያለዕድሜ ጋብቻ፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ያልተፈለገ እርግዝና፣ ደህንነቱን ያልተጠበቀ የጽንስ ማቋረጥ፣ ወሲባዊና ጾታዊ ጥቃቶች፣ የኤች አይቪ ኤድስና አደንዛዥ ዕጾች ከሚያደርሱት ጉዳት መጠበቅ እንደሚገባም ገልጸዋል። ከዚህ አንጻር ዓለም አቀፉ የቤተሰብ ዕቅድ ፌዴሬሽን እርግዝናቸውን ማዘግየት ለሚፈልጉ ሴቶችና ወንዶች የወሊድ መቆጣጠሪያ አገልግሎት መጠቀም የሚያስችላቸውን ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል። የመውለድ ችግር ያለባቸው ወንዶችና ሴቶች የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ እንደሆነም ነው ሚስ ማሪ ያስረዱት። በአጀንዳ 2063 የመጀመሪያ አፈጻጸም ሪፖርት በአፍሪካ የእናቶች ሞት እ.አ.አ በ2013 ከነበረበት 341  እ.አ.አ በ2019 ወደ 269 ቀንሷል። በተመሳሳይ ወቅት በኢትዮጵያ የነበረው የእናቶች ሞት መጠን ከ676 ወደ 412 ቀንሷል። ይህ ውጤት የተገኘው የዓለም አቀፉ የቤተሰብ ዕቅድ ፌዴሬሽንና የአፍሪካ አገራት ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት እንደሆነ ሚስ ማሪ አስረድተዋል። ዓለም አቀፉ የቤተሰብ ዕቅድ ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ የፌዴሬሽኑ አባል ከሆነችበት እ.አ.አ 1971 ጀምሮ የአገሪቷ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት እንዲሻሻል የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል። እ.አ.አ ከ2019 ጀምሮ ለሶስት ዓመት የሚቆይ በእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብርና ሌሎች አጋሮች በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ማሻሻል ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት እየተተገበረ ነው። ለፕሮጀክቱ ትግበራ በየዓመቱ ከ800 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍም እያደረገ ይገኛል። እንደ ሚስ ማሪ ገለጻ ፌዴሬሽኑ ከኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር ጋር በቅንጅት በመስራት ከፋይናንስ ድጋፍ ባለፈ የስልጠናና የቴክኒክ ድጋፎችንም እያደረገ ነው። በዚህም በኢትዮጵያ ያለው የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት መሻሻል እንደታየበትና ዘላቂነት እንዲኖረውም ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል። የአፍሪካ አገራት የቤተሰብ ዕቅድን በተመለከተ በብሔራዊ ዕቅዶቻቸው ያስቀመጧቸው ግቦች ትግበራ ላይ ያለባቸውን የአፈጻጸም ችግር ለመቅረፍ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። በአፍሪካ ለሚከናወኑ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ስራዎች የፋይናንስ ድጋፍ ከለጋሽ ድርጅቶች የሚገኝ እንደሆነ የገለጹት ሚስ ማሪ የአፍሪካ አገራት ለስራው ቋሚ በጀት በመመደብ ዘላቂነት ያለው ስራ መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል። ፌዴሬሽኑ በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ያለውን ተቋማዊ አደረጃጀት፣ ስርዓትና አቅም ማጠናከር እ.አ.አ በ2020 በአፍሪካ ለመስራት ያሰበው ዋነኛ ተግባሩ እንደሆነም አክለዋል። የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማኅበር የፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ሀብቴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በማህበሩ በኩል እ.አ.አ ከ1971 የፌዴሬሽኑ አባል ከሆነችበት ጊዜ አንስቶ በየዓመቱ ወደ አንድ ሚሊዮን ዶላር ገደማ የበጀት ድጋፍ እያገኘች ነው ብለዋል። በተገኘው ድጋፍ የእናቶችና ህጻናትን ጤና ለማሻሻል የግንዛቤ ማስጨበጥና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት የማስፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል። በዚህም በኢትዮጵያ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ነው የተናገሩት። በ2011 ዓ.ም ከ16 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን 10 ሺህ የሚሆን ያልተፈለገ እርግዝናንም ማስቀረት ተችሏል ብለዋል። ያም ሆኖ ስለ ቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ያሉ የአመለካከት ችግሮችና በቤተሰብ ዕቅድ ላይ የተዘጋጁ ሰነዶችን የአፈጻም ክፍተት ማረም ትኩረት የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ ጠቁመዋል። በዘላቂ የልማት ግቦች ውስጥ ግብ 5 ሴቶች፣ ህጻናትና ልጃገረዶችን ከግጭት፣ ካልተፈለገ እርግዝና መጥፎ ተግባራት ነጻ እንዲሆኑ የሚደረግበትን ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት ያስቀምጣል። በመግለጫው ላይም የዓለምና አፍሪካ አገራት ለዚህ ግብ ውጤታማነት ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸውም ተገልጿል። የዓለም አቀፉ የቤተሰብ ዕቅድ ፌዴሬሽን /አይ.ፒ.ፒ.ኤፍ/ የአፍሪካ ዳይሬክተር ሚስ ማሪ-ኢቭሊን ፔትሩስ-ባሪ በ33ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ለመሳተፍና በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ የካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ይታወሳል። ከሁለት ወራት በፊት የፌዴሬሽኑ ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት ሚስ ማሪ ከኢትዮጵያ በፊት ሴኔጋልና ናይጄሪያን ጎብኝተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም