ቀጥታ፡

ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ጋር ባደረግነው ውይይት ችግሮቻችን እንደሚፈቱ ተስፋ ጥለናል - የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ተወካዮች

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 6/2012 በወቅታዊ የአገራቸው ጉዳይና ስለሚኖሩበት ሁኔታ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ያደረጉት ውይይት እንዳስደሰታቸው በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ምሽት በመካከለኛው ምስራቅ ከሚገኙ አገራት ከተውጣጡ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል። ኢትዮጵያዊያኑ በውይይታቸው ወቅታዊውን የአገራቸውን ሁኔታ የተመለከቱ ጥያቄዎች እንዲሁም እንዲፈቱላቸው የሚፈልጓቸውን ችግሮቻቸውን በማቅረብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መክረዋል። ኑሯቸውን አቡዳቢ ያደረጉት ወይዘሮ እስከዳር ታደሰ 'መንግስታችን ያለንበት ድረስ መጥቶ ሲያናግረን ይህ ተደርጎ የማያውቅ ነገር በመሆኑ ጥልቅ ደስታ ፈጥሮብናል ይላሉ። አቶ ሽፈራው አባካ የሻርጃ ነዋሪ ናቸው 'አይደለም በሰው አገር አገርህ ላይ ሆነህ እንኳን መሪህን በአካል አግኝተህ ስለ ችግሮችህ መወያየት ትልቅ ስሜት ይፈጥራል' ነው ያሉት። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ ለማየትና ሊያወያዩን ስለመጡ "ከልብ እናመሰግናቸዋለን" ብለዋል። ለችግሮቻችን መፍትሄ እንደምናገኝ በተለይም በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ችግር ሰምተው መፍትሄ እንደሚሰጡበት እምነት አለኝ ያሉት ደግሞ የሻርጃ ነዋሪዋ ወይዘሮ ውብዓለም ተፈራ ናቸው። ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ያመቻቹት የነጻ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚዋ ተማሪ ሄለን ታደሰ ነች። ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቀውን የትምህርት ዕድል በማግኘቷ የተሰማትን ደስታ ገልጻ በሳይበር ደህንነት ቴክኖሎጂ ዕውቀት ገብይታ አገሯን ለማገልገል እንደምትፈልግ ገልጻለች። በተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች የዚያድ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ መስራች ዶክተር አብዮት ምንዳዬ ማኅበረሰቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማግኘት ስለነበረው ጉጉት አንስተዋል። በዚያ በሚኖሩ ዜጎች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን የፖሊሲ ለውጥ የሚያስፈልጋቸው ካሉ በመለወጥ እንዲሁም ከመንግስታቱ ጋር በመነጋገር እንዲፈቱላቸው ያላቸውን ፍላጎትም ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ ከአቡዳቢ ወደ ዱባይ በማቅናት ከ10 ሺህ በላይ ከሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም