ቀጥታ፡

የብልጽግና እሳቤ ከቁስ ባለፈ በውጭ ለሚኖሩ ዜጎች ክብር ትኩረት ይሰጣል - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 6/2012 የብልጽግና እሳቤ ቁስ ማካበት ብቻ ሳይሆን በውጭ አገራት የሚኖር ሁሉም ዜጋ ክብሩና መብቱ እንዲጠበቅ መስራትም ጭምር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። የብልጽግና እሳቤ ቁስ ማካበት ብቻ ሳይሆን በውጭ አገራት የሚኖር ሁሉም ዜጋ ክብሩና መብቱ እንዲጠበቅ መስራትም ጭምር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። በተበታተነ ሁኔታ ሳይሆነ በተደራጀ መልኩ ኢንቨስት ለማድረግ ዝግጁ ለሆኑ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ትናንት ምሽት በመካከለኛው ምስራቅ ከሚገኙ አገራት ከተውጣጡ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ነው። የውይይቱ ተሳታፊዎችም በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አቅርበዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔርን ተገን በማድረግ እየታየ ያለው ግጭትና ክፍፍል መቅረት አለበት፤ በቤተ እምነቶች ላይ ጥቃት የሚያደርሱ አካላት በሕግ ሊጠየቁ ይገባል የሚሉ ሃሳቦችም በስፋት ተንጸባርቀዋል። መንግስት በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ኢንቨስት የሚያደርጉበትን ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥርም ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው በኢትዮጵያ የክርስትናና እስልምና ተከታዮች ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ የአብሮነት እሴት ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን አስታውሰዋል። ነገር ግን በብሔር ከፋፍለው አብሮነታችንን ለማጥፋት ሞክረው ያልተሳካላቸው ኃይሎች አሁን ላይ በሃይማኖት በኩል እየሞከሩ ነው ብለዋል። መንግስት አጥፊዎችን ለህግ እያቀረበ መሆኑን ጠቁመው፤ ሁሉም ዜጋ ከመንግስት ጎን በመቆም ይህን እኩይ ተግባር ሊታገል እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በአቡዳቢ የሚኖሩ ክርስቲያን ኢትዮጵያዊያን ለረዥም ጊዜ ሲያነሱት የቆዩት የቤተ እምነት ግንባታ ፈቃድ ጥያቄ በመንግስት ሰፊ የዲፕሎማሲ ጥረት ምላሽ ማግኘቱንም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ጎዳና እያቀናች መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የብልጽግና እሳቤም ቁሳዊ ሃብትን ከማካበት ባለፈ ለዜጎች ክብር ተግቶ መሰራትን ያካትታል ብለዋል። "መንግስት በጉዳዩ ላይ በትኩረት ለመስራቱ ደግሞ እናንተ ምስክሮች ናችሁ" ሲሉ ነው የገለጹት። በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሰብሰብ ብለው በአገራቸው ኢንቨስት በማድረግ በአገራቸው ኢኮኖሚ ላይ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል። በዚህ መልኩ ተደራጅተው ለሚመጡ ዲያስፖራዎች ቢሯቸው ሁሌም ክፍት መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩት። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ ረፋድ ላይ ከአቡዳቢ ወደ ዱባይ በማቅናት ከ10 ሺህ በላይ ከሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ጋር እንደሚወያዩም ይጠበቃል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም