ቤተክርስቲያኒቷ እየገጠሟት ያሉትን ችግሮች መፍታት ያለብን የቤተክርስቲያኗ አባላት ነን - ብፁዕ አቡነ ማትያስ - ኢዜአ አማርኛ
ቤተክርስቲያኒቷ እየገጠሟት ያሉትን ችግሮች መፍታት ያለብን የቤተክርስቲያኗ አባላት ነን - ብፁዕ አቡነ ማትያስ
አዲስ አበባ ( ኢዜአ) የካቲት 5/2012 ''ቤተክርስቲያኒቷ እየገጠሟት ያሉትን ችግሮች መፍታት ያለብን እኛ ራሳችን የቤተክርስቲያኗ አባላት ነን'' ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ገለጹ። ''መንግስት ህግና ስርአትን የማስከበር ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አለበት'' ብለዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን "በጎውን ማን ያሳያናል?" በሚል ርዕስ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያዘጋጀችው የፓናል ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በቤተክርስቲያኒቷ ላይ እየደረሱ ያሉ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባበሱ መጥተዋል። "እየተከሰቱት ያሉት ችግሮች ማንም አላመጣቸውም ከኛው ነው የመጡት ስለዚህ እኛው ራሳችን ያሉትን ችግሮች ተወያይተን መፍታት አለብን" ብለዋል ፓትርያርኩ። በቤተክርስቲያኗ ላይ እየደረሰ ያለው ችግር የቆየ መሆኑን ያስታወሱት ብጹዕነታቸው፤ የችግሩ መፍቻ ቁልፍ መወያየት እንደሆነ አመልክተዋል። ''አብያተ ክርስቲያናትን ማቃጠል ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ነው፤ ሃይማኖትን የማክበር መብት ሊከበር ይገባል'' ብለዋል። በቤተክርስቲያኗ ላይ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ እየደረሰባት ያለው ፈተና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና ለዚህም መፍትሔው ችግርን በውይይት መፍታት መሆኑን አመልክተዋል። መንግስትም ህግና ስርዓት የማስጠበቅ ሃላፊነቱን በአግባቡ በመወጣት ህግ የሚጥሱ አካላትን ለፍትሕ ማቅረብ እንዳለበትም ፓትርያኩ አሳስበዋል። የተዘጋጀው የውይይት መድረክ ባሉት ችግሮች ላይ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት የሚኖረው ሚና ወሳኝ እንደሆነና ምዕመኑ በአንድነት በጋራ ተሰብስቦ ችግሮችን ለመፍታት መስራት እንደሚገባው አክለዋል።
የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የታሪክ መምህር ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ ቤተክርስቲያኗ አሁን እየገጠማት ላለው ችግር ከምትሰጠው መፍትሔ ባለፈ ዘላቂ ተቋማዊ መፍትሔ ማበጀት እንዳለባት አመልክተዋል። በከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ የቤተክርስቲያኗ ሊቃውንቶች፣ ብጹአን አባቶችና ቅዱሳን አባቶች የችግሩን መፍቻ ሃሳብ ማፍለቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል። ከዚህ ባሻገርም በቤተክርስቲያኗ ላይ የሚሰነዘር ጥቃትን ለመከላከል መንግስት ህግ የማስከበር ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል። ቤተክርስቲያኗ ታሪኳን፣ ትውፊቷንና እሴቷን ለወጣቱና ለእምነቱ ተከታይ ለማስተላለፍ የሚያሰችል የታሪክ ጥናት ተቋም እንድታቋቁም ምክረ ሃሳብ ሰንዝረዋል። የውይይት መድረኩ ታዳሚ የሆነው ምዕመን ወጣት አብርሃም ሃይሌ ወጣቶች ስሜታዊ ሳይሆኑ ቤተክርስቲያኗን የመጠበቅ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል። ቤተክርስቲያኗ የገጠማትን ፈተና ለመወጣት በቃል የሚነገሩትን የመፍትሔ ሀሳቦች ወደ ተግባር መቀየር ከሁሉም የቤተክርስቲያኒቷ አባላት የሚጠበቅ ነው ብሏል። በውይይት መድረኩ ላይ በተለያዩ ባለሙያዎች የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። የሃይማኖት አባቶች፣ ምዕመናንና ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በፓናል ውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።