ቀጥታ፡

የካርጎ አገልግሎትን ለማዘመን የሚያስችል የልምድ ልውውጥ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2012 በአዲስ አበባ ከ23 አገሮች የተውጣጡ ባለሙያዎች የካርጎ አገልግሎትን ለማዘመን የሚያስችል የልምድ ልውውጥ  እያካሄዱ ነው።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ አቪየሽን አካዳሚ ከ23 አገሮች የተውጣጡ 60 ባለሙያዎች በካርጎ አገልግሎት ዘርፍ ያለውን ተግዳሮትና ምርጥ ተሞክሮ የሚለዋወጡበት መድረክ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎና ሎጂስቲክስ ዋና ሃላፊ አቶ ፍጹም አባዲ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ መድረኩ በአደገኛ ሸቀጦች አያያዝ ዙሪያና በካርጎ እንቅስቃሴ ላይ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ያለመ ነው።

በተለይ በአስተሻሸግና በአያያዝ ችግር በሰው፣ በእንስሳትና በእጽዋት እንዲሁም በአየር ንብረት ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት የልምድ ልውውጡ ትልቅ ፋይዳ  እንዳለው ተጠቅሷል።

''ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቋ የካርጎ ኦፕሬተር በመሆኗ ያላትን ተደራሽነት ለማስፋት የአገልግሎት ጥራትን የበለጠ ለማሳደግ መድረኩ ከፍተኛ እገዛ አለው'' ብለዋል።

አለም ዓቀፉ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ማህበር ያወጣውን መስፈርት አገሮች አሟልተው የንግድ ልውውጥ እንዲያደርጉ መድረኩ ወሳኝ እንደሆነም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እያንዳንዳቸው 100 ቶን ማንሳት የሚችሉ 12 የጭነት ማመላለሻ አውሮፕላኖች እንዳሏት የገለጹት አቶ ፍጹም፤  አለም ዓቀፉ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ማህበር ያወጣውን መስፈር አሟልታ በ130 መዳረሻዎች በዓመት 450 ሺህ ቶን ሸቀጥ እንደምታመላልስም ተናግረዋል።

የዓለም ዓቀፉ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ማህበር የካርጎ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ ሚስተር አንድሬ ማጀርስ እንዳሉት፤ አገሮች የካርጎ አገልግሎትን ለማዘመን ህግና ስርዓትን አክብረው መንቀሳቀስ አለባቸው።

በዓለም ላይ በየዓመቱ ከ5 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ቶን በላይ ሸቀጥ በአየር ትራንስፖርት እንደሚነገድ ገልጸው፤ ከሸቀጥ አያያዝ ጉድለትና ከአስተሻሸግ ጥራት ማነስ የሚመጣን ችግር ለመፍታት ልምድ መለዋወጥ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአለም ዓቀፍ ደረጃ ታዋቂ አየር መንገድ በመሆኑ የካርጎ አሰራርን ለማዘመን በሚደረገው የልምድ ልውውጥ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም ገልጸዋል።

ዓለም ዓቀፉ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ማህበር ከኢትዮጵያ አቪየሽን አካዳሚ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም