ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙኃን ድንገተኛ የጤና አደጋዎችን ሲዘግቡ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው - ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ( ኢዜአ) የካቲት 5/2012 መገናኛ ብዙኃን በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚከሰቱ ድንገተኛ የጤና አደጋዎችን ሲዘግቡ በሳይንሳዊ መረጃ ተመስርተው በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ። ሚኒስቴሩ የመገናኛ ብዙኃን የጤና ፎረምን በአዳማ ከተማ እያካሄደ ነው። የኅብረተሰብ ድንገተኛ ጤና አደጋዎች በድንገት የሚከሰቱ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ተጠቃሽ ነው። በሚኒስቴሩ የጤና ኤክስቴንሽንና የመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ የጤና ማበልጸግና አጠባበቅ አስተባባሪ አቶ አምላክ አለልኝ ለኢዜአ እንዳሉት፤ መገናኛ ብዙኃን የኅብረተሰብ ድንገተኛ ጤና መረጃ ለሕዝብ ሲያደርሱ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። ''የድንገተኛ አደጋ መረጃ ኅብረተሰቡን በማያደናግጥ መልኩ መቅረብ ይገባዋል'' ብለዋል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በዓለም ላይ የሚከሰቱ ድንገተኛ አደጋዎች በጉዳዩ ላይ የጠራ ግንዛቤ ሳይኖራቸው መረጃ ለኅብረተሰቡ በማድረስ ረገድ ጉድለት እንደሚታይባቸው ገልጸዋል። ይህንን ለመከላከል በሚኒስቴሩ በኩል መረጃ እንዴትና በማን ለኅብረተሰቡ መድረስ እንዳለባቸው የሚተነትኑ መርጃ  መሣሪያዎች፣ መመሪያዎችና ሌሎች የጤና ትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን መጠቀም እንደሚችሉ አመልክተዋል። አደጋዎቹ ሲከሰቱ መርጃ መሣሪያዎችንና መመሪያዎችን በመጠቀም ሳይንሳዊ ጥበብ በተሞላበት መንገድ መገናኛ ብዙሃኑ መዘገብ እንደሚገባቸው አስተባባሪው ገልጸዋል። የህብረተሰቡን ጤና ለማስጠበቅ በተለይም ወረርሽኝ ሲያጋጥም የጥንቃቄ መልዕክት ፈጥነው እንዲያስተላልፉ አስገንዝበዋል። በቻይናዋ ዉሃን ከተማ ተቀስቅሶ ለዓለም ስጋት የሆነውን የኮሮና ቫይረስና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን የተመለከተ መረጃ ለማህበረሰቡ ፈጥኖ ማድረስ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ''ሚኒስቴሩና በጤና ዘርፍ የተቋቋመው የመገናኛ ብዙኃን ፎረም በሽታውን አስመልክቶ ግንዛቤ ለመፍጠርና የተጣራ መረጃ ለማቅረብ ያግዛል'' ተብሏል። ፎረሙ ከተመሰረተ ሶስት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ መገናኛ ብዙኃን በጤና ዙሪያ የሰሯቸውን ዘገባዎች አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ፎረም ሚኒስቴሩ ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር በሚሰራባቸው መንገዶች ላይ ይመክራል። ጤናማ ማህበረሰብን መፍጠር ዓላማ አድርጎ የተቋቋመው ፎረም የኤሌክትሮኒክ፣ የኦንላይን፣ የኅትመትና ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትን በአባልነት ያካተተ ሲሆን፣ በየሩብ ዓመቱ እየተገናኘ ሥራዎችን ይገመግማል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም