ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ቀልጣፋ አገልግሎት ለሰጡ ተቋማትና ባለሙያዎች ሽልማትና እውቅና ተሰጠ

ድሬደዋ ሰኔ 20/2010 በድሬዳዋ አስተዳደር ለሕብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ኃላፊነታቸውን ለተወጡ ግንባር ቀደም ተቋማትና ባለሙያዎች እውቅናና ሽልማት ተሰጠ። በድሬዳዋ 12ኛው የፐብሊክ ሰርቪስ ሳምንት በዓልን አስመልክቶ ትናንት የእውቅናና የምስጋና ሥነ-ሥርዓት ተዘጋጅቷል። የድሬዳዋ ፐብሊክ ሰርቪስ የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ  አቶ ሀርቢ ቡህ እንደገለጹት በአገር አቀፍና በድሬዳዋ እየተመዘገበ ለሚገኘው ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ እድገት ሠራተኛው ግንባር ቀደም ድርሻ አላቸው። በአስተዳደሩ ህዝቡ የጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ተወጥተው ግንባር ቀደም ውጤት ላስመዘገቡ 47 ተቋማትና ግለሰቦች እውቅናና የምስክር ወረቀት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ አቶ ሀቢብ እንዳሉት ካይዘንን በተለያዩ የአስተዳደሩ ተቋማት ትምህርት ቤቶች መተግበር በመቻሉ የውስጥ አሰራርን በማቀላጠፍ ውጤታማ የንብረት አያያዝና አገልግሎት አሰጣጥን ማስፈን ተችሏል። ከእዚህ በተጨማሪ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የህዝብና የመንግስት ሃብትን ከብክነት ለማዳን መቻሉን ነው የገለጹት። በሀገር አቀፍ ደረጃ በአገልግሎት ሰጪና በትምህርት ተቋማት የካይዘን አመራር ፍልስፍና አጣጥሞ በመተግበር በኩል ድሬደዋ የመጀመሪያ ለመሆን መቻሏንም ገልጸዋል። "ግንባር ቀደም የሆኑ ሠራተኞችና ተቋማትን ክብርና እውቅና መስጠት መልካም አስተዳደር ለማስፈን የሚያስችሉ የለውጥ መሳሪያዎችን በተቀናጀ መንገድ ለመተግበር ያግዛል " በልዋል፡፡ በመድረኩ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ኡስማን በበኩላቸው አርአያ ለሆኑት የተሰጠው ክብርና እውቅና ተሸላሚዎች ይበልጥ እንዲበረታቱና ሌሎችም እነሱን እንዲከተሉ ከማስቻሉ በተጨማሪ በድሬዳዋ መልካም አስተዳደርን በተሸለ ደረጃ ለማስፈን የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በህዝቡ ዘንድ ምሬትና ቅሬታዎችን እየፈጠሩ ባሉ የመሬት ልማት፣ የገቢ፣ የውሃ ፍሳሽ፣ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትና መሰል ተቋማት የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን ትርጉም ባለው መንገድ ለመፍታት የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም  አሳስበዋል፡፡ ከጤና ባለሙያዎች ሞዴል ሠራተኛ ሆነው የተሸለሙት አቶ መስፍን ጌታቸው እውቅናው የበለጠ ለመስራት እንዳነሳሳቸው ተናግረው፣ በቀጣይ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ርህራሄ የተሞላበት ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እንደሚተጉ ገልጸዋል፡፡ " በቅንነት ህዝቡን ማገልገል ክብር ነው "  በሚል መርህ የተከበረውን የሲቪል ሰርቪስ ሳምንት ምክንያት በማድረግ ለግንባር ቀደምና ሞዴል ሰራተኞችና ተቋማት የተዘጋጁትን የምስክር ወረቀቶች የሰጡት የድሬዳዋ አስተዳደር አፈ-ጉባኤ አብዱልሰላም አህመድ፣ ምክትል ከንቲባ አብደላ አህመድና ሌሎችም የካቢኔ አባላት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ጨምሮ የተሰሩ ተግባራትን ለህዝብ በማሳወቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የተወጡ የሚዲያ ተቋማትም ተሸላሚ መሆናቸው ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም