ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ኤክሳይዝ ታክስ አዋጅን አፀደቀ

አዲስ አበባ ( ኢዜአ) የካቲት 5/2012 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 5ኛ አመት የስራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የተሻሻለው የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅን በአብላጫ ድምፅ አፀደቀ። በምክር ቤቱ ኤክሳይዝ ታክስን በተመለከተ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1186/2012 ሆኖ በአብላጫ ድምፅ፣ በአራት ተቃውሞና በሰባት ድምፀ ተአቅቦ አጽድቆታል። የምክር ቤቱ አባላት የኤክሳይዝ ታክስ ላይ በተደረጉ ማሻሻያዎች ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል። የፈረስ ጉልበታቸው ከ1 ሺህ 300 ሲሲ ያልበለጡ ተሽከርካሪዎችና ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ላይ የነበረው የኤክሳይዝ ታክስ ማስተካከያ ከተደረገባቸው ማሻሻያዎች ውስጥ አንዱ ነው። በዚህም መሰረት በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪ እንዲገጣጠሙ ሙሉ በሙሉ ተበትነው የቀረቡ፣ አዲስ በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪ እንዲገጣጠሙ በከፊል ተበትነው የቀረቡና አዲስ ሙሉ በሙሉ ተገጣጥመው የቀረቡ ተሽከርካሪዎች የኤክሳይዝ ታክስ ከ30 በመቶ ወደ 5 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል። በተሽከርካሪዎቹ የአገልግሎት መጠን ልክ ከዚህ ቀደም ከነበረው የ25 በመቶ ቅናሽ የተደረገ ሲሆን ከሰባት አመት የበለጠ ያገለገሉት ተሽከርካሪዎች ከ430 በመቶ ወደ 405 በመቶ የኤክሳይዝ ታክሱ ዝቅ እንዲል ተደርጓል። በፕላስቲክ ጠርሙስ ውሃ አሽጎ በመሸጥ ላይ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች የፕላስቲክ ጠርሙስ በአካባቢ ደህንነት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ አንዳንድ እርምጃዎች እየወሰዱ በመሆኑ በታሸገ ውሃ ላይ ተጥሎ የነበረው የኤክሳይዝ ታክስ ከነበረበት 15 ወደ 10 በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉም ተገልጿል። የምክር ቤቱ አባላት ''ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ሲባል ተጥሎ የነበረው የኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያ የተደረገበት ምክንያት ግልፅ አይደለም'' የሚል ጥያቄን አንስተዋል። ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው ኤክሳይዝ ታክስ ከፍ ያለበት ምክንያት የአካበቢ ብክለትን ለመቀነስ፣ የአገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታትና ዜጎች የሚያወጡትን ተጨማሪ ወጪ የሚያስቀር መሆኑ ተነግሯል። የምክር ቤቱ አባላት የጨርቃጨርቅ ምርቶች መሰረታዊ በመሆናቸው ኤክሳይዝ ታክስ መጣሉ ኀብረተሰቡ ላይ ጫና ስለማሳደሩ ጠይቀዋል። በሌላ በኩል ደግሞ አገር በቀል እውቀቶች ጥበቃ ስለሚያስፈልጋቸውና ጥበቃ ለማድረግ ሲባል በገቢ ጨርቃጨርቅ ምርቶች የሚጣለው ኤክሳይዝ ታክስ ከፍ ማለት እንዳለበት የሚገልጽ ሀሳብ ከምክር ቤቱ አባላት ተንፀባርቋል። በሲጋራ ላይ የተጣለው የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ አሁንም ዝቅተኛ እንደሆነ በመግለጽ ሀሳባቸውን ያንጸባረቁት የምክር ቤቱ አባላት፤ 'በአካባቢ ደህንነት ላይ እየሰሩ ይገኛሉ' በሚል በታሸገ ውሃ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ሌሎች ተቋማት ጥያቄ እንዲያነሱ አያደርግም ወይ የሚሉ ጥያቄዎች አንስተዋል። የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ለምለም ሀድጉ በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ በተሽከርካሪዎች ላይ የተደረገው ማሻሻያ በአዲስ ተሽከርካሪዎች መሰረት የተደረገ ማሻሻያ ነው። አዲስ ተሽከርካሪዎች ይጣልባቸዋል ተበሎ የነበረው ኤክሳይዝ ታክስ ከ30 በመቶ ወደ 5 በመቶ ዝቅ በመደረጉ የሚጣለውን ኤክሳይዝ ታክስ ተመጣጣኝ ለማድረግ ታስቦ 25 በመቶ ዝቅ ማለቱን አብራርተዋል። በጨርቃጨርቅ ምርት ላይ የተጣለው ኤክሳይዝ ታክስ ናይለን፣ ሹፈን፣ ብርድልብስና የመሳሰሉት ላይ መሆኑንና የአገር ውስጥ አምራቾች የሚጠቀሙበት ፈትልን እንደማይመለከት ጠቅሰዋል። ምርቶች በበቂ መጠን መመረት እስኪችሉ ድረስ በጨርቃጨርቅ ላይ የሚጣለው የኤክሳይዝ ታክስ 8 በመቶ ሆኖ እንደሚቀጥልና በበቂ መጠን ሲመረት ከፍ ሊል እንደሚችልም አስረድተዋል። ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው ከኤክሳይዝ ታክስ በተጨማሪ የተፈናቀሉ ሰዎችን ጥበቃና ድጋፍ የማድረግ የአፍሪካ ህብረት የካምፓላ ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል። ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን ህጋዊ ሰውነት ለመስጠትና የማህበረሰብ ልማት፣ አስተዳደርና አጠቃቀም የተመለከቱ ረቂቅ አዋጆችን ለዝርዝር እይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም