መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሞጣ መስጊዶች ማሰሪያና ለተጎጂዎች ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሞጣ መስጊዶች ማሰሪያና ለተጎጂዎች ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ቀረበ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 5/2012 የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሞጣ መስጊዶች ማሰሪያና ለተጎጂዎች ላደረገው ድጋፍ ምስጋናውን አቀረበ። በገቢ ማሰባሰብ ሂደቱ እስካሁን ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡም ታውቋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እንድሪስ በሰጡት መግለጫ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሞጣ መስጊዶች ማሰሪያና ለተጎጂዎች ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል። በሞጣ ከተማ ለተቃጠሉ መስጊዶች ማሰሪያና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ማቋቋሚያ እስካሁን በገንዘብ ብቻ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል። የተደረገው ድጋፍ አንድነትና ጠንካራ ወንድማማችነትን የሚያሳይ መልካም ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል። ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በተፈጸመው ጥቃት አራት መሥጊዶች መቃጠላቸውና በአካባቢው በንግድ ተቋማት ላይ ዝርፊያና ቃጠሎ መፈፀሙ ይታወሳል። በመሆኑም ምክር ቤቱ ይህን ችግር ለማቃለልና ተጎጂዎቹን ለማቋቋም 200 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። ሆኖም በአገር ውስጥ ብቻ በጥሬ ገንዘብ 208 ሚሊዮን 939 ሺህ 962 ብር መሰብሰቡን የምክር ቤቱ ዋና ጸሀፊና የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ሃጂ ቃሲም መሀመድ ተናግረዋል። የተለያዩ ወገኖች ወርቅ ፣ብር፣ ባጃጅና የሞባይል ቀፎዎችን ጨምሮ ከ750 ሺህ ብር በላይ በአይነት መለገሳቸውንም እንዲሁ። በውጭ ሀገራት የተደረገው ገቢ የማሰባሰብ ስራ ምክር ቤቱ በከፈተው የዶላር አካውንት ተጠናቆ ገቢ እንዲደረግም ምክር ቤቱ ጠይቋል። ከዛሬ ጀምሮ በሞጣ ተጎጂዎች ስምም ሆነ በምክር ቤቱ ስም ምንም አይነት የገቢ ማሰበሰብ ስራ አለመኖሩንም ጠቅላይ ምክር ቤቱ አስታውቋል።