ቀጥታ፡

የተመኙትን ሀብት በአገራቸው ሰርተው እንዳገኙት ከስደት ተመላሾች ገለፁ

ማይጨው ኢዜአ የካቲት 05/12 ዓ/ም--- ከርቀት ሲመኙት የነበረውን ሀብት በቅርበት በአገራቸው ሰርተው እንዳገኙት በትግራይ ደቡባዊ ዞን በመስኖ ልማት የተሰማሩ የራያ አዘቦ ወረዳ ከስደት የተመለሱ አርሶ አደሮች ገለጹ። አርሶ አደር ፈረጃ አብዱልቃድር በራያና አዘቦ ወረዳ የገነቴ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ለተሻለ ኑሮ ከአራት ዓመት በፊት በህገወጥ መንገድ ወደ ባእድ አገር ተሰደው እንደነበር ያስታውሳሉ ። በስሜት ተገፋፍተው የተትረፈረፈ ሀብት የማካበት ህልም አንግበው የስደት መንገድ ቢመርጡም ከአራት ዓመታት የስደት ቆይታ በኋላ ወደ አገራቸው የተመለሱት ግን ስቃይንና መከራን በመግፋት ከ80 ሺህ ብር ያልበለጠ ገንዘብ ብቻ ይዘው መሆኑን ይናገራሉ ። ከስደት መልስ በትውልድ ቀያቸው የመስኖ ልማት ስራ በማከናወን በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ 150 ሺህ ብር ገቢ ከማግኘታቸው ባሻገር ለሌሎች ወጣት አርሶ አደሮች የስራ እድል መፍጠራቸውን አስረድተዋል ። የአራት ዓመት የስደት ቆይታቸው ከንቱ ልማትና ቅዥት እንደነበር የገለፁት አርሶ አደር ፈረጃ ከርቀት ሲመኙት የነበረውን ሀብት በቀያቸው ጥረው ግረው በቅርበት እንዳገኙት ተናግረዋል ። ወጣቱ ትውልድም ህገ ወጥ ስደት ከማሰብ ይልቅ በተወለደበትና ባደገበት አካባቢ ያለውን ሀብት በአግባቡ ተጠቅሞ ህይወቱን መቀየር እንደሚችል ከእኔና መሰል ከስደት ተመላሾች መማር አለበት ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል ። ሌላው ከስደት ተመላሽ አርሶ አደር ጀዋር መሓሪ በበኩላቸው ’’የአካባቢየን እምቅ ሃብት ሳላይ ወደ ህገ ወጥ ስደት ማቅናቴ ከእንግልትና ስቃይ ውጪ ያተረፈልኝ አንዳች ጥቅም የለም ’’ ባይ ናቸው ። በተሰማሩበት የመስኖ ልማት በሄክታር እስከ 800 ኩንታል ድረስ የቲማቲም ምርት እያገኙ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ጃዋር አሁን ከ50 በላይ ለሚሆኑ ወጣት አርሶ አደሮች ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር መቻላቸውን ገልጸዋል። የወረዳው ተወላጅ የሆኑት አርሶ አደር ሲራጅ ባዳሲ በበኩላቸው የስደት ህይወት መምረጣችን ለበርካታ አመታት ሀብት እንዳናፈራና ጥሩ ህይወት እንዳንመራ ጋርዶብን ቆይቷል ይላሉ ። "በአካባቢያችን ያለውን እምቅ ሀብት ሳልንቅ በትጋት በመስራቴ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ከመገንባት በተጨማሪ ሀብት ማፍራት ጀምሬያለሁ " ያሉት አርሶ አደር ሲራጅ ደግሞ የስደት ህይወት አሰቃቂ በመሆኑ ሲያስቡት ጭምር እንደሚያንገሸግሻቸው ተናግረዋል ። የትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ሓላፊ ዶክተር አትንኩት መዝገቡ በበኩላቸው በአርሶ አደሮች ደረጃ ከመስኖ ልማት በሄክታር 800 ኩንታል ቲማቲም ማምረት መቻሉ ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል። ይህ ውጤትም የሁሉም አካላት የቅንጅት ስራና የመደጋገፍ ውጤት ነው ብለዋል። በመስኖ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች የዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። በራያ አዘቦ ወረዳ 5 ሺህ 500 ሔክታር መሬት በመስኖ እየለማ ሲሆን በልማት ስራው ከ8 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ከወረዳው የግብርናና ገጠር ልማት ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም