ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ጸጥታ መስፈን ወሳኝ ሚና አላት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ጸጥታ መስፈን ወሳኝ ሚና አላት
አዲስ አበባ የካቲት 5/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ጸጥታ መስፈን ወሳኝ ሚና እንዳላት በጣሊያን የሳንት ኤጂዲዮ ማህበረሰብ ኢንስቲትዩት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከፍተኛ አማካሪ ጂያንካርሎ ፔንዛ ተናገሩ። 33ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ለመታደም በአዲስ አበባ የተገኙትና በቀጣናው የተለያዩ ጥናቶችን ያካሄዱት ጂያንካርሎ ፔንዛ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የአፍሪካ አህጉር የኢኮኖሚ ገጽታ እየተቀየረ ነው። ኢኮኖሚውን ከማሻሻል ጎን ለጎን የአህጉሩን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ስራዎች መሰራት እንዳለበትም ጠቁመዋል። መንግስታት ሰላምን ለማስጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት ከተለያዩ አካላት ጋር ተቀናጅተው ቢሰሩ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያመለከቱት ጂያንካርሎ ፔንዛ፤ በተለይም ህብረተሰቡን ማሳተፍ ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል። ከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል እየመጣ ያለው 'መንግስታት ሰላምን ለማስጠበቅ ይስሩ' የሚለው ግፊት ለአህጉሩ ሰላምና ጸጥታ በጎ ተጽዕኖ እንዳለውም ተናግረዋል። የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን በተመለከተም የኢትዮጵያ ሚና ወሳኝ መሆኑን ነው የተናገሩት። በተለይም የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ሰላማዊ መሆኑ የቀጣናውን የሰላም ተስፋ ያለመለመ መሆኑን ገልጸዋል። የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ) ውስጥ ባላት ቆይታ ያዳበረችውን ልምድ መጠቀም እንዳለባትም ጠቁመዋል። የኢጋድ 13ኛው የመሪዎች ጉባኤ ባለፈው ህዳር ወር በአዲስ አበባ ሲካሄድ ላለፉት 11 ዓመታት በኢጋድ ሊቀ-መንበርነት የቆየችው ኢትዮጵያ ቦታውን ለሱዳን ማስረከቧ ይታወሳል። ኢጋድ ለአካባቢው ሰላምና ደህንነት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ኢጋድ በቀጣናው ሰላምና ፀጥታ እንዲረጋገጥ ለማድረግ ከሚሰራው ስራ አልፎ ልማትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ እየሰራም ይገኛል። ቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን ለማፋጠን የመተዳደሪያ ደንቡን በማሻሻል በቅርቡ ወደ ስራ ለመግባት እንቅስቃሴ መጀመሩም ይታወቃል። የኢጋድ አባል አገሮች በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በቀውስ አያያዝና ግጭት አፈታት ዙሪያ አመርቂ ስራ እየሰሩ ሲሆን የደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እንዲሁም በኢትዮጵያና ኤርትራ ዙሪያ የተሰሩ የሰላም ስምምነት ስራዎች ይጠቀሳሉ።