የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ የመረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው ረቂቅ አዋጅ ጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ የመረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው ረቂቅ አዋጅ ጸደቀ
አዲስ አበባ ( ኢዜአ) የካቲት 5/2012 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጥላቻ ንግግርና ሃሰተኛ መረጃ ማሰራጨትን ለመከላከል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ጨምሮ ስምንት አዋጆችን አጸደቀ። ምክር ቤቱ 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን ዛሬ አካሂዷል። በዚህም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ይጋፋል የሚሉ አከራካሪ ሃሳቦች የተነሱበት የጥላቻ ንግግርና ሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ነበር። የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ አዋጁን መርምሮ ለምክር ቤቱ ያቀረበ ሲሆን፣ በህገ መንግስቱ የተደነገጉ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶችን ይጋፋል የሚሉ የመከራከሪያ ሃሳቦች ከምክር ቤት አባላት ተነስተዋል። የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግለሰቦችና ቡደኖችን፣ የሃይማኖት፣ በብሄር፣ በዘር፣ በጾታ፣ በአካል ጉዳተኞችን መሰረት ያደረገ የጥላቻና ሃሰተኛ መረጃ ስርጭት በህግ ለመቆጣጠር ህጉ አስፈላጊ ነው የሚሉ ሃሳቦችም ተንፀባርቀዋል። የጥላቻና ሀሳተኛ መረጃ ጉዳይ ሕጋዊ መፍትሔ ካልተበጀለት ለአገር ሰላምና ደህንነት ከፍተኛ ስጋት መሆኑም ተጠቁሟል። የኢፌዴሪ ሕገ መንግስትና ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውና ያጸደቀቻቸውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ጠብቆ የተቀረፀውን አዋጅ ከነማሻሻያው ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል። አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ግን ረቂቅ አዋጁ በህገ መንግስቱ የተመላከቱ ሃሳብን በነጻነት የማንሸራሸር መብቶችን የሚሸረሽር፣ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን የሚጻረር ነው በማለት ተከራክረዋል። ከዚህ በፊት በነበሩ ውይይቶች ረቂቅ አዋጁ በበርካቶች የተተቸ ስለመሆኑም ከምክር ቤት አባላት ተነስቷል። ከምክር ቤቱ አባላት ከዚህ ቀደም ሲተገበር እንደነበረው የፀረ ሽብር ህግ፣ ዜጎች በማንነታቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይደርስባቸው ሲሉ ስጋታቸውን የገለፁ አሉ። "ጥላቻን የማይቃወም የጥላቻ ነጋዴ ብቻ እንጂ" ህገ መንግስቱ ዜጎች ተከባብረው በአብሮነት እንዲኖሩ እንደሚያትት በመግለጽ አዋጁ ካልዘገዬ በስተቀር ማጽደቅ ይገባናል የሚል ሃሳብም በተቃራኒው ተነስቷል። በሕግ መንግስቱም ሆነ ኢትዮጵያ በተቀበላቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሃሳበን በነጻነት የመግለጽ መብቶች ሊገደቡባቸው የሚችሉ ልዩ ሁኔታዎች እንዳሉ በመጥቀስ፣ ረቂቅ አዋጁም በዚህ የተቃኘ መሆኑን አስረድተዋል። ምክር ቤቱ ከዚህ በፊት የአንድ ግለሰብ ጥቅማ ጥቅም ለማስከበርና ለመሻር ሲባል አዋጆችን ሲያጸድቅ መቆየቱን በመግለጽ፣ አሁን ግን ለአገርና ለህዝብ አደጋ የሚጥል ድርጊትን ለመከላከል የወጣ አዋጅ መሆኑን አስረድተዋል። በድጋፍና ተቃውሞ በምክር ቤት አባላት ክርክር የተደረገበት ይኸው አዋጅ፣ በመጨረሻም በ23 ተቃውሞ፣ በ2 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል። በአዋጁ ከተመላከቱት መካከል የጥላቻ ንግግርን በአደባባይ ስብሰባ፣ በሕትመት፣ በብሮድካስት፣ በማህበራዊ ሚዲያና መሰል ዘዴዎች በጽሁፍ፣ በምስል ወይም በቪዲዮ ማሰራጨት ይከለክላል። ይህን ተላልፎ የሚፈፅም ካለ የሁለት ዓመት እስራት ወይም የ100 ሺህ ብር ቅጣት የሚጠብቀው ይሆናል። በጥላቻ ንግግሩ ሳቢያ በግለሰብ ወይም ቡደን ጥቃት ከተፈጸመም ከአንድ አስከ አምስት ዓመት እስራት ተጥሏል። በተመሳሳይ የሃሳብ ማስተላለፊያ ስልቶች ሃሰተኛ መረጃን ያሰራጨና በተሰራጨው ሃሰተኛ መረጃ ሁከት ወይም ግጭት ከተከሰተ መረጃውን ያሰራጨው አካል ከ2 እስከ 5 ዓመት እስራት ይጠብቀዋል። ከ5 ሺህ በላይ ተከታይ ባለው የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ወይም ብሮድካስት እና በየጊዜው በሚወጣ ህትመት ውጤት የተሰራጨ የሃሰት መረጃ ከሆነም እስከ ሶሰት ዓመት እስራትና ከ100 ሺህ ብር ያልበለጠ ቅጣት ይኖረዋል። ምክር ቤቱ የኤክሳይዝ ታክስ፣ የፌዴራል የአስተዳደር ስነ ስርዓትና የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች እውቅና የመስጠትና የመፈጸም ስምምነት ረቂቅ አዋጆችንም አጽድቋል። በተመሳሳይ ለዓይነ ስውራንና የእይታ ችግር ላለባቸው ሰዎች የቀለም ጽሁፍ ሕትመት ስራዎችን ተደራሽ ለማድረግ የወጣውን የማራካሽ ስምምነት፣ የአፍሪካ አረጋዊያን መብቶች ፕሮቶኮል ስምምነት፣ በአገር ውስጥ ለተፈናቀሉ ሰዎችን ጥበቃ ድጋፍ ለማድረግ የተፈረመውን የአፍሪካ ሕብረት የካምፓላ ስምምነት ረቂቅ አዋጆችንም አጽድቋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትን ሕጋዊ ሰውነት ለመስጠት የቀረበን ረቂቅ አዋጅና የማህበረሰብ ተፋሰሶች ልማት፣ አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጆችን ደግሞ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።